Home > Articles > የአባይ ግድብ – እና- የወታደራዊ ጥቃት ዕቅድ

የአባይ ግድብ – እና- የወታደራዊ ጥቃት ዕቅድ

October 8, 2012

MINILIK SALSAWI 

የአቶ መለስን ዜና ዕረፍት ተከትሎ ደግሞ ሰሞኑን ትኩረት የሚስብ መረጃ ብቅ ብሏል፡፡ ይኸው የዊኪሊክስ ድረ ገጽ የለቀቀው መረጃ ግብፅ የህዳሴውን ግድብ ለመምታት የሚያስችላትን የጦር ሠፈር ሱዳን ውስጥ ለማቋቋም ፈቃድ መግኘቷን የሚያመላክት ነው፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዓላማም በዚሁ ዘገባ ላይ በመመሥረት አንዳንድ ሐሳቦችን መሰንዘር ነው፡፡ ስለሆነም ጽሑፉ መጠነኛ የመከራከሪያ ነጥቦችን ከማንሳት ያለፈ ጥልቅ የሆነ ትንተና የመስጠት ዓላማ የለውም፡፡ ግብፅ የተባለውን ‹‹መጠባበቂያ ዕቅድ›› (Contingency Plan) እንዴትና ለምን ተግባር ላይ ማዋል እንደሚያስፈልጋት ከመነጋገራችን በፊት የግድቡን አንድምታ በመጠኑ መዳሰስ ያስፈልጋል፡፡

የህዳሴው ግድብ አንድምታ
ለረዥም ዘመናት የዜሮ ድምር ፖለቲካ ሲከተሉ የኖሩት የግብፅ መሪዎች ያልተረጋጋችና ደካማ ኢትዮጵያን ለማየት ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ዓባይ ላይ የምትገነባውን ማንኛውንም ግድብ እንደሚመቱ ሲዝቱ መቆየታቸው የታወቀ ነው፡፡ አገራችንም ወንዙን ለመገደብና ለጥቅሟ ለማዋል ያላት ፍላጐት ሲንፀባረቅ የአሁኑ የመጀመርያ አይደለም፡፡ የአሁኑን ወቅት ልዩ የሚያደርገው ግን ግብፅ ከሱዳን ጋር ሚስጥራዊ ስምምነት ላይ የደረሰች መሆኗ መዘገቡና አገራችንም የግድቡን ፕሮጀክት በመሬት ላይ እየተገበረች ያለችበት ወቅት መሆኑ ነው፡፡

አገራችን በተናጠል (Unilaterally) የግድብ ፕሮጀክቷን ይፋ ለማድረግ የተገደደችው ግብፅ ወደ ጋራ የስምምነት ማዕቀፍ እንድትመጣ የሚደረገው ጥረት መቋጫ ባለማግኘቱ እንደሆነ ከማንም የተሰወረ አይደለም፡፡ በእርግጥ ግድቡ ለኃይል ማመንጫ ብቻ የሚውል በመሆኑና ውኃውም እየገባ የሚወጣ በመሆኑ ለረዥም ጊዜ የውኃውን መጠን የሚቀንሱ እንደማይሆን የዘርፉ ምሁራን ይገልጻሉ፡፡ በትነት አማካይነት ይባክናል ተብሎ ከሚጠበቀው የውኃ መጠንና ለወደፊቱ ለመስኖ እርሻ ጥቅም ላይ ሊውል ይችላል የሚለው ሥጋት እንደተጠበቀ ሆኖ ማለቴ ነው፡፡

እስካሁን በዋናነት የሚታየው መሠረታዊ እንቅፋት ግን የአካባቢው አገሮች የኃይል ሚዛን መቀየር ከሚፈጥረው ሥጋት የሚመነጭ ነው፡፡ በተጨማሪም ግድቡ ኢትዮጵያን የአካባቢው የኃይል ምንጭ (Regional Power House) ስለሚያደርጋት የአካባቢውን አገሮች ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለማፋጠን ትጠቀምበታለች የሚል እምነት ያሳድራል፡፡ በትክክልም ግድቡ እንደታሰበው ከተጠናቀቀ የአገራችንን ፖለቲካዊ፣ ዲፕሎማሲያዊና ኢኮኖሚያዊ ጡንቻ ማፈርጠሙ ስለማይቀር፣ የተዳከመች ኢትዮጵያን ማየት ከሚፈልገው ልማዳዊና ግትር አስተሳሰብ ጋር በቀጥታ መላተሙ አይቀሬ ነው፡፡ ከዚህ ዓይነቱ የኃይል ትስስር ግብፅም ተጠቃሚ የምትሆንበት ዕድል ቢኖርም የግብፅ የፖለቲካ ልሂቃን ግን ይህንን ዕድል ወደ ጐን እንደሚገፉት በተደጋጋሚ አሳይተዋል፡፡ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ የግብፅን ሉዓላዊነት ለኢትዮጵያ ተገዥ ማድረግ እንደሆነ ተደርጐ ስለሚወሰድ ነው፡፡ ስለሆነም መሠረታዊው ችግር ከአሮጌው አስተሳሰብ በመላቀቅ ከአዲሱና ከማይቀለበሰው እውነታ ጋር መላመድ ካለመቻል የሚመጣ አባዜ መሆኑ እሙን ነው፡፡

ይህ አሮጌ አስተሳሰብ በብዙ አቅጣጫ ፈተና እየገጠመው እንደሆነ መገንዘብ አያዳግትም፡፡ በተይም የላይኛው ተፋሰስ አገሮች በፊርማቸው እየተቀበሉት የሚገኘው የጋራ የስምምነት ሰነድ ተጠቃሽ ነው፡፡ በክቡር አቶ መለስ ዜናዊ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ ከፕሮቶኮል ደንብ ወጣ ባለ መልኩ ንግግር ያደረጉት የኡጋንዳው ፕሬዚዳንት ሙሴቬኒ አጽንኦት ሰጥተው የተናገሩትም ስለ ዓባይ ወንዝ ነበር፡፡ የግብፁ ጠቅላይ ሚኒስትር ሂሻም ቃንዲልና የሱዳኑ ፕሬዚዳንት ሐሰን አልበሽር በታደሙበት በዚህ ታሪካዊ ቀን ሙሴቪኒ ቁራጭ ማስታወሻ ከደረት ኪሳቸው በማውጣት፣ ግዙፍ የቆዳ ስፋትና የሕዝብ ብዛት ያላት አገራችን የምታመርተውን እዚህ ግባ የማይባል የኤሌክትሪክ ኃይል መጠን ከትንሿ እንግሊዝ ጋር በማወዳደር፣ ከቁጥር ስሌት በላይ የሆነውን ፖለቲካዊ መልዕክታቸውን በበቂ ሁኔታ አስተላልፈዋል፡፡ ባለፈው ዓመት በባህር ዳር ከተማ በተካሄደው የጣና ፎረም ስብሰባ ወቅት አቶ መለስ በዚያው አቅራቢያ ትልቅ ግድብ እያሠሩ መሆኑን እንደነገሯቸው በማስታወስ የሰውየውን ራዕይ ከማሞገስ አልፈው ተተኪያቸው በዚያው መንገድ እንዲገፋበት በአደባባይ መክረዋል፡፡ በጥቅሉ ኢትዮጵያም ሆነች ኡጋንዳ ወደ አዲስ ምዕራፍ እየተሸጋገሩ መሆኑን አስምረውበት አልፈዋል፡፡ ይህ ዓይነቱ ግልጽ አቀራረብ ለአሮጌው ትርክት መሞት አመላካች ነው፡፡

እንዳለመታደል ሆኖ ሱዳንም ከላይ የተጠቀሰው አባዜና አሮጌ አስተሳሰብ ሰለባ እንደሆነች ይገመታል፡፡ የሱዳን የፖለቲካ ልሂቃን ጥልቅ የሆነ የኃይል (Energy) ትስስር አገራቸውን የኢትዮጵያ ጥገኛ የሚያደርግ የብሔራዊ ደኅንነት ሥጋት አድርገው እንደሚቆጥሩት በስፋት የሚነገር ጉዳይ ነው፡፡ ትስስሩ ሱዳን ነዳጅ፣ ኢትዮጵያም የኤሌክትሪክ ኃይል በማቅረብ ላይ የመተሠረተ ቢሆንም፣ ለኢትዮጵያ የኃይል አቅራቢነት ዕውቅና መስጠት ግን እንደ ተንበርካኪነት እንደሚወስዱት ይታመናል፡፡ ይህ እንግዲህ የሱዳን ነዳጅ ዘይት አቅርቦት የኢትዮጵያን እጅ ለመቆልመም ያለው አቅም ደካማ ነው ብሎ ከማመንና የሱዳንን የተናጠል ተጋላጭነት ከመፍራት የሚመነጭ ደንቃራ አስተሳሰብ መሆኑ ነው፡፡

በኃይል ሚዛኑ ላይ ከሚኖረው ተፅዕኖ ባሻገር ሱዳን በግዛቷ ለመገንባት ለምታስባቸው አነስተኛ የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች አስፈላጊነት ላይ በረዶ የሚቸልስና ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ መሆኑ ደግሞ ሌላው ችግር ነው፡፡ እነዚህ ፕሮጀክቶች ግን የሱዳንን ኢኮኖሚ ለመመገብ ያላቸው አስተዋጽኦ አነስተኛ እንደሆነ ቢታወቅም፣ የኃይል ሚዛን መዛባትን በማስወገድ ላይ በተንጠለጠለው አስተሳሰብ ምክንያት በአገራችን ላይ የሚኖራቸውን ጥገኝነት ለማስቀረት እስከቻሉት ድረስ መታተራቸው አይቀርም፡፡ ስለሆነም በሱዳን በኩልም ያለው አመለካከት የአገራችንን ጠንካራ ሆኖ መውጣት መከላከል ላይ የተመሠረተ እንደሆነ መገመት አያዳግትም፡፡ በእርግጥ አንድ አገር በጐረቤቷ ተፅዕኖ ሥር እንዳትወድቅ መፈለግ በራሱ ትልቅ ችግር ባይሆንም፣ ዋናው መሠረታዊ ጉዳይ ግን ይህ ዓይነቱ ፍላጐት የተመሠረተበት አመክንዮ ትክክለኛነት መሆኑ አያጠራጥርም፡፡

የወታደራዊ ጥቃት ዕቅድ አሳማኝነትና ስሌቱ
እኛ ኢትዮጵያውያንንና ምናልባትም ግብፃውያንንና ሱዳናውያንን እያነጋገረ ያለው የዊኪሊክስ መረጃ ምንጭ መቀመጫውን አሜሪካ ካደረገው ዝነኛው የስለላ ተቋም ስትራትፎር (Stratfor) መሆኑ በዘገባው ተጠቅሷል፡፡ ግብፅ እንደ ‹‹መጠባበቂያ ዕቅድ›› ይዛዋለች የተባለው ይኸው የጦር ሠፈር የሚቋቋመው ምዕራብ ዳርፉር ውስጥ ኩርሲ የተባለ ቦታ ላይ መሆኑን ሰምተናል፡፡ የቀረቡት ሁለት የጥቃት አማራጮችም በተዋጊ የጦር ጄቶች ግድቡን መምታት ወይም በልዩ ኮማንዶ ጦር የግድቡን ሥራ ማስተጓጐል ወይም ሙሉ በሙሉ ማክሸፍ ነው፡፡

ይህንን ዘገባ የግብፅ ባለሥልጣናት ፈጥነው ‹‹የፈጠራ ወሬ›› መሆኑን ቢገልጹም፣ ይህ ዓይነቱ ምላሽ ግን ከአገራዊ ጥቅም አንፃር የሚጠበቅና ተገቢም መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሆኖም ግን ይህንን ማስተባበያ እንደ መተማመኛ መውሰድና የዊኪሊክስን መረጃ ሙሉ በሙሉ ማጣጣል ውጥረት በተሞላበትና አለመተማመን በሰፈነበት ክፍለ አኅገር ወስጥ የሚመረጥ አካሄድ አይሆንም፡፡ ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው የኢትዮጵያን ግድብ እንመታለን የሚለው አቋም በጋማል አብዱል ናስርና በአንዋር ሳዳት ጊዜም የነበረ እንጂ አዲስ አይደለም፡፡ ለበርካታ ዓመታት የቆየ ዛቻ በመሆኑ ብቻ ግን ጉዳዩን ወደ ሥነ ልቦና ጦርነት ደረጃ አያወርደውም፡፡ ምክንያቱም አገራችን በዓባይ ወንዝ የመጠቀም መብቷን እውን የሚያደርግ ፕሮጀክት ከምኞት ወደ ተጨባጭ ተግባር እየቀየረች ነውና፡፡ ይህ ዓይነቱ ‹‹ዕቅድ›› ካለ ግን ግድቡን እንደገና ለማስከለስ ወይም እንዲዘገይ ለማድረግ የሚያስችል ኃይል ይኖረዋል የሚል አመለካከት ግብፅ ውስጥ አይኖርም ብሎ መከራከር አይቻልም፡፡

ዊኪሊክስ ከዚህ መረጃ ሌላ በሊባኖስ አየር ክልል ላይ በአወዛጋቢ ሁኔታ በድንገት ስለተከሰከሰው የኢትዮጵያ አየር መንገድም መረጃ አሰራጭቷል፡፡ መቼም ቀድሞውንም ቢሆን የአደጋውን መንስዔ አስመልክቶ የሊባኖስ መንግሥት ያወጣውን ሪፖርት ፈጥኖ ያጣጣለው የኢትዮጵያ መንግሥት መረጃውን በጥሞና መከታተሉ አይቀሬ ነው፡፡ እስካሁን ባለው ሁኔታም በዓለም አቀፍ ደረጃ ዊኪሊክስ የተቀላጠፈ የመረጃ ልውውጥን አደናቅፏል ተብሎ ሲብጠለጠል እንጂ የተሳሳተ መረጃ አሰራጭቷል ተብሎ ሲወነጀል አልሰማንም፡፡

ስለሆነም በህዳሴው ግድብ ላይ የወጣውን መረጃ ተንተርሶ በፖለቲካዊም ሆነ በወታደራዊ ሁኔታዎች ላይ መወያየትና ሐሳብን መግለጽ የ‹‹ጦርነት ነጋሪት›› እንደመጐሰም ተደርጐ ሊወሰድ አይገባውም፡፡ መንግሥት ይህንን ጥሬ መረጃ ከማራገብ ተቆጥቦ የራስን ሥራ ‹‹ሙያ በልብ›› ብሎ አድፍጦ እንዲሠራ የሚያደርገው በቂ አመክንዮ ቢኖርም፣ እኛ ተራ ዜጐች ግን በጉዳዩ ላይ ብንከራከር ከቶውንም ቢሆን ስህተት ሊሆን አይችልም፡፡

ሁኔታው እየበሰለና እየደረጀ ከሄደ ደግሞ ከሁሉም አማራጮች በኋላ በሚከሰተው የከፋው ሁኔታ (Worst Case Scenario) ላይ መዘጋጀት የዜጐችም የመንግሥትም ግዴታ መሆኑ አይቀሬ ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ1990ዎቹ መገባደጃ አካባቢ ‹‹ኤርትራ አትወረንም›› በሚል አስተሳሰብ ላይ የተመሠረተው የመንግሥት አቋም ምን ያህል ዋጋ እንዳስከፈለን የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ የሚያዋጣው መንገድ ተገቢውን የቤት ሥራ እያከናወኑ ‹‹ውሾች ይጮሃሉ፣ ግመሎች ግን ጉዟቸውን ቀጥለዋል፤›› በሚለው የግብፃውያን ብሂል መመራት ነው፡፡

ይህ ሁሉ መረጃ የተለቀቀውና የመወያያ አጀንዳ የሆነው ግድቡ በታችኛው ተፋሰስ አገሮች ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተፅዕኖ በጋራ እየተጠናና ውጤቱ ባልታወቀበት ሁኔታ ነው፡፡ አገራችንም የተፋሰሱ አገሮች ስምምነትን ፊርማ ለማጠናቀቅ የምታደርገውን ግፊት በገታችበት ወቅት ላይ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የግብፅ ባለሥልጣናት በአገራችን ባለፈው ዓመት ጉብኝት ካደረጉ በኋላና አቶ መለስ ዜናዊም በግብፅ ምድር ተገኝተው የግብፃውያንን ጥቅም ጉዳት ላይ እንደማይጥሉ ማረጋገጫ ከሰጡ በኋላ መሆኑ ነው፡፡

እ.ኤ.አ ከ1995 ወዲህ በአፍሪካ የመሪዎች ስብሰባ ላይ መገኘትን እርግፍ አድርገው የተውት ሆስኒ ሙባረክ ጀርባቸውን እንደሰጡን ከሥልጣን ወርደዋል፡፡ በምትካቸው የተመረጡት ፕሬዚዳንት መሐመድ ሙርሲ ግን በተመረጡ በጥቂት ጊዜያት ውስጥ አዲስ አበባ ላይ በተካሄደው የመሪዎች ስብሰባ ላይ ለመሳተፍ መምጣታቸው ይታወቃል፡፡ ሆኖም ግን ክቡር አቶ መለስ ዜናዊ በሕክምና ላይ የነበሩ በመሆናቸውና ለውይይት ዕድል ሳያገኙ መቅረታቸው በዓባይ ወንዝ ላይ ለሚደረገው ዲፕሎማሲ አንድ ጉድለት መሆኑን መካድ አይቻልም፡፡ አቶ መለስ አምና ግብፅን በጐበኙበት ወቅት በሥልጣን ላይ የነበሩት የሽግግሩ ዘመን ጠቅላይ ሚኒስትር እንጂ መሐመድ ሙርሲ በሕዝባዊ ምርጫ ወደ ሥልጣን አልመጡም ነበር፡፡

ፕሬዚዳንት ሙርሲ ለጉዳዩ ለሰጡት አትኩሮት ማሳያ የሚሆነው ግን በአቶ መለስ የቀብር ሥነ ሥርዓት ላይ የቀድሞውን የመስኖና የውኃ ሀብት ሚኒስትርና የአሁኑን ጠቅላይ ሚኒስትር እንዲገኙ መላካቸው ነው፡፡ ሆኖም ግን የአቶ መለስ ዜናዊ ዕረፍት ይፋ ከመሆኑ በፊት አንዳንድ የግብፅ ባለሥልጣናት ‹‹ከተተኪው አመራር ጋር በትብብር እንሠራለን›› በማለት መናገራቸው ትኩረትን መሳቡ አልቀረም፡፡ በዚህ ጸሐፊ እምነት ይህ ዓይነቱ የተቻኮለ አገላለጽ አገራችን በዓባይ ላይ የያዘችው ጠንካራ አቋም የአቶ መለስ የግል ‹‹ጀብደኝነት›› የፈጠረው ለማስመሰል የታለመ ነው፡፡ አለበለዚያ በጋራ ለመሥራት የሚያስችለውን የዲፕሎማሲ ምኅዳር አቶ መለስ ስለማጥበባቸው ምንም መረጃ የለም፡፡ በርካታ ግብፃውያን ሆስኒ ሙባረክን የዓባይን ፖለቲካ ያለአግባብ በማጦዝና አላስፈላጊ ምስል በመፍጠር እንደሚወነጅሏቸው ሁሉ፣ በተመሳሳይ ሁኔታ አቶ መለስ የህዳሴውን ግድብ ያለአግባብ ለራሳቸው ፖለቲካዊ ፍላጐትና የመሪነት አሻራ (Legacy) ለመተው ተጠቅመውበታል ለማለት የሚደፍሩ የግብፅ ልሂቃን እንደሚኖሩ አያጠራጥርም፡፡

ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት የዚህ ጽሑፍ መነሻ የዊኪሊክስ መረጃ እውነት ቢሆንም በሚል እሳቤ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር መሠረታዊው ጉዳይ የተባለው ወታደራዊ ጥቃት ሊተገበር የሚችልበትን ወታደራዊና ፖለቲካዊ ሁኔታዎች መፈተሽ ያስፈልጋል፡፡ የመጀመርያው አማራጭ ተደርጐ ሊቀርብ የሚችለው በተዋጊ ጄት ግድቡን ማጥቃት ነው፡፡ ግብፅና ኢትዮጵያ ድንበር የማይጋሩ አገሮች በመሆናቸው ግብፅ ለረዥም ጊዜ የቆየ ዛቻዋን ለመተግበር ሦስተኛ አገርን ወይም ዓለም አቀፍ የባህር ወሰንን መጠቀም እንዳለባት እሙን ነው፡፡ በህንድ ውቅያኖስ ወይም በቀይ ባህር ላይ በመሆን ከመርከብ የሚወነጨፉ ረዥም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳይሎችን (Long Range Missiles) መጠቀም ደግሞ ሌላኛው አማራጭ ነው፡፡ ሦስተኛው መንገድ ደግሞ በተራራማ ቦታዎች ሠልጥኗል የሚባልለት ቅልብ ኮማንዶ ጦርን ከሦስተኛ አገር በመነሳት የኢትዮጵያን ድንበር አቋርጦ ጥቃት እንዲያደርስ ማስቻል ይሆናል፡፡

አሁን የቀረበው መረጃ ግን የጦር ጄቶችን ወይም ልዩ ኮማንዶ ኃይልን መጠቀም የሚል በመሆኑ በዚሁ ላይ እናተኩር፡፡

በመጀመርያ ደረጃ የተባለው የጦር ሠፈር ከኢትዮጵያ አዋሳኝ ከሆነው ምሥራቅ ሱዳን ይልቅ በምዕራብ ዳርፉር አካባቢ መሆኑ ሌሎች ውስጣዊ ምክንያቶች እንደተጠበቁ ሆነው ሁለት መሠረታዊ ነገሮችን ታሳቢ ያደረገ ሊሆን ይችላል፡፡ አንደኛው የጦር ሠፈሩን በኢትዮጵያ ድንበር አቅጣጫ በኩል ማቋቋም በኢትዮጵያ ላይ ግልጽና ቀጥተኛ አደጋ የሚፈጥር እንዳይሆን በማሰብና በዚህም ምክንያት የሚፈጠረውን እሰጥ አገባ ለመቀነስ ሊሆን ይችላል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ጦር ሠፈሩ በምሥራቅ አቅጣጫና በግድቡ አቅራቢያ ከሆነ ከኢትዮጵያ ጦር ኃይል ጋር በቀጥታ ሊፈጠር የሚችለውን ፍጥጫ ለማስወገድ ይሆናል፡፡

የህዳሴው ግድብ ከሱዳን ድንበር እምብዛም እንደማይርቅ የታወቀ ነው፡፡ ስለሆነም ማንኛውም የአየር ጥቃት የኢትዮጵያን የአየር ክልል ማቋረጥ የግድ ይሆንበታል፡፡ በእርግጥ የኃይል ማመንጫ ግድብ እንደ ኑክሌር ጣቢያ ከመሬት በታች የተቀበረ ባለመሆኑ በግልጽ የሚታይ ዒላማ መሆኑ መይካድም፡፡ መቼም ቢሆን ግን ‹‹ወታደራዊ ዒላማ›› ተብሎ ሊገለጽ አይችልም፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን የአገራችንን የአየር ክልል ማቋረጡ ከባዱ ፈተና ይሆናል፡፡ ለማንኛውም ይህ ዓይነት አማራጭ በግድቡ ላይ መጠነ ሰፊ ጉዳት ለማድረስና ተመልሶ አገልግሎት እንዳይሰጥ ለማምከን የሚያነጣጥር በመሆኑ የግድቡ የተወሰነ ምዕራፍ ከተጠናቀቀ በኋላ የሚከናወን ሊሆን ይችላል፡፡
ዝርዝሩን ለወታደራዊ ባለሙያዎች እንተወውና እንደ ተራ ዜጋ የምናውቀው ግን በግድቡ አቅራቢያ ቀደም ሲል በወታደራዊው መንግሥት የተገነባ ዘመናዊ የጦር ጄቶች ማረፊያ በባህር ዳር ከተማ መኖሩን ነው፡፡ ስለሆነም አሁንም ሆነ ወደፊት የዊኪሊክስ መረጃ እውነትም ሆነ አልሆነ የዚህን ጦር ሠፈር አቅም ከማናጠከር ውጭ አማራጭ የለም፡፡

በሁለተኛነት አማራጭ ተደርጐ የቀረበው የኮማንዶ ጦር በማስገባት ጥቃት መፈጸም የሚለው ‹‹ዕቅድ›› ነው፡፡ ይህ እንግዲህ ለዓመታት ስንሰማው የነበረውንና ግብፅ በተራራ ውጊያ ስልት የሠለጠነ ኮማንዶ ጦር ባለቤት ናት ከሚለው መረጃ ጋር አብሮ የሚሄድ ነው፡፡ ዓላማው ቢለያይም ይህ ዓይነቱ የጥቃት ‹‹ዕቅድ›› አሜሪካ በፓኪስታን ግዛት ውስጥ ቢን ላደንን ለመምታት ከተጠቀመችበት ስልት ጋር ይመሳሰላል፡፡ ይህ ዓይነቱ ጥቃት በተዋጊ ሔሊኮፕተሮችና በልዩ ኮማንዶ እገዛ በጨለማ ውስጥ ሊከናወን ይችል ይሆናል፡፡ ከዘዴዎቹ መካከልም በግድቡ ወሳኝ ክፍሎች ላይ ከባድ ፈንጂዎች ማጥመድን ሊያካትት ይችላል፡፡ ይህ ዓይነቱ አማራጭ አጥቂውን ወገን ብዙ ዋጋ የሚያስከፍልና ምናልባትም የመሳካት ዕድሉ የመነመነ እንደሚሆን ለመገመት የግድ ወታደራዊ ጠበብት መሆን አይጠይቅም፡፡ ያም ሆነ ይህ የኮማንዶ ጦር ሰርጐ ገብነትን ለመከላከል የሚያስችል በቂ አቅም እንደሚኖር መገመት አይከብድም፡፡

ከዚህ የኮማንዶ ጦር ጋር መታየት ያለበት ተዛማጅ ጉዳይ በግድቡ ሥራ የሚሳተፉ ድርጅቶችንና ግለሰቦችን በመጠቀም ሊከናወን የሚችለው የአሻጥር ሴራ (Sabotage) ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ሴራ ቀደም ብሎ በሚከናወን ውስብስብ የስለላ ተግባር (Espionage) የሚካሄድ ሊሆን እንደሚችል ይታወቃል፡፡ ይህ ዓይነቱን ሴራ ከሌሎች የሚለየው ከውጭ በሚገቡ መሣርያዎች ላይ አሻጥር ከመሥራት ጀምሮ ለስለላ ሥራ በዋናነት ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎችንና የጥበቃ ሠራተኞችን ጭምር በመመልመል እስከመጠቀም የሚደርስ ሊሆን ይችላል፡፡ በማንኛውም አገር ዜጐች ለውጭ አገር ጠላት በቅጥረኝነት ሊሠሩ የሚችሉባቸው የተለያዩ መቀስቀሻዎች (Motives) ቢኖሩም የገንዘብ ክፍያ አብዛኛውን ድርሻ እየያዘ የመጣ መሆኑ አያከራክርም፡፡

ስለሆነም በደፈናው የተወሰኑ የአንድ አገር ዜጎች ብሔራዊ ጥቅማቸው ላይ ተደራድረውና ቅጥረኛ ሆነው አገራዊ ጉዳት አያደርሱም ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው፡፡ ይህ ሁኔታ በየጊዜው በተለያዩ አገሮች የሚያጋጥም ክስተት ነው፡፡ ለማንኛውም ይህ መንገድ እጅግ ውስብስብና ይህንን ሴራ የምታቀናብረውን አገር ሚና የሚያድበሰብስና በግልጽ እንዳይታይ የሚያደርግ በመሆኑ ብርቱ ጥንቃቄ የሚያስፈልገው እንደሆነ አያጠራጥርም፡፡ ስለሆነም ለዚህ ብቸኛው መከላከያ መንገድ የፀረ ስለላ (Counter-espionage) አቅምን በማጠናከርና እስካሁንም የተለያዩ የሽብር ሴራዎችን ሲያከሽፍ የኖረውን የስለላ መዋቅር ማስፋፋትና ዘመናዊ ማድረግ ብቻ ነው፡፡

በአጠቃላይ የሁሉም ‹‹ዕቅዶች›› ዓላማ ፕሮጀክቱ ውጤታማ እንዳይሆን በማድረግ በኢትዮጵያውያን ዘንድ ብዙ እየተዘመረለት ያለው የህዳሴው ግድብ የ‹‹ብሔራዊ ውርደት›› ምልክትና የ‹‹ትውልድ ኪሳራ›› ሆኖ እንዲቀር ማድረግ እንደሚሆን መገመት አያስቸግርም፡፡ በተይም ከላይ እንደተጠቀሰው አገራችን በክፍለ አኅጉሩ ተገቢው ቦታ እንዳይኖራት ከመፈለግ የሚመነጭ ነው፡፡

የሱዳን የስሌት አጣብቂኝ
ቀደም ሲል እንደጠቀስኩት ሌላው መሠረታዊ ጉዳይ የጦር ሠፈሩን ለማስተናገድ ተስማምታለች የተባለችው ሱዳን ምን ትርፍና ኪሳራ ይኖራታል የሚለው ነው፡፡ በመጀመርያ የሱዳንንና የግብፅን ግንኙነት በጥቅሉ ብናየው በአብዛኛው አመርቂ ሊባል የሚችል አይደለም፡፡ ቡዛንና ዌቨር የተባሉ የዓለም አቀፍ ፀጥታ አጥኚዎች ‹‹Regions and Powers›› በሚለው መጽሐፋቸው የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ‹‹አንዳንዴ ውጥረት፣ አንዳንዴም ወዳጅነት›› የተሞላበት እንደሆነ ይከራከራሉ፡፡ ታዋቂው የአፍሪካ ቀንድ የፖለቲካ ተንታኝ አሌክስ ዲዋል ደግሞ እ.ኤ.አ በ1989 በጄኔራል አልበሽር የተመራው ብሔራዊ እስላማዊ ግንባር (National Islamic Front) ሥልጣን ከተቆናጠጠ ጀምሮ ሱዳንን ከግብፅ ጥላ ሥር ነፃ አውጥቷታል ይላል፡፡ ይህም የሱዳን ልሂቃን ለዓመታት ከተጠናወታቸው የበታችነትና የጠባቂነት አባዜ ለመላቀቅ የነበራቸውን ፍላጐትና ራሳቸውን ከግብፅ ለማራቅ የነበራቸውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው፡፡ እ.ኤ.አ በ1995 አዲስ አበባ ላይ አል ጋማል እስላሚያ የተባለው የግብፅ አክራሪ ቡድን በሆስኒ ሙባረክ ላይ ያካሄደውን የግድያ መኩራ ያቀነባበሩትን ግለሰቦች ሱዳን መጠለያ ለመስጠት የነበራትን አቋም ማሳየቷ አንድ ምልክት ነው፡፡

አሁን ግን በግብፅ ሙስሊም ወንድማማቾች ወደ መንበረ ሥልጣኑ ብቅ እያለ በመሆኑ ለሁለቱም አገሮች ግንኙነት አዲስ ምዕራፍ ይከፍት ይሆናል፡፡ እንደሚታወቀው የግብፅ ወንድማማቾች ለዘመናት በኃይል ሲጨፈለቅ የሱዳኑ የወንድማማቾች ንቅናቄ ግን ከሞላ ጐደል የፖለቲካ ሥልጣንን ተቆናጥጦ የሚገኝ ነው፡፡ የሱዳን ወንድማማቾች የግብፅ ወንድማማቾች ንቅናቄ ውላጅ መሆኑና በተመሳሳይ እስላማዊ ቀኖናዎች የሚመራ መሆኑ የታወቀ ነው፡፡ ግብፅ በሕዝባዊ አመፅ በምትናጥበት ወቅት በደቡብ ሱዳን መገንጠል ምክንያት ሕዝባዊ ተቃውሞ ይቀጣጠላል ተብሎ ቢጠበቅም ሊሆን አልቻለም፡፡ ተቃዋሚውና ዝነኛው የሃይማኖት ምሁር ሐሰን አልቱራቢም ባለፈው ዓመት የአልበሽርን መንግሥት በሕዝባዊ ንቅናቄ እንደሚጥሉት ቢዝቱም ህልማቸውን ወደ ተግባር ለመቀየር ተስኗቸዋል፡፡ ያም ሆነ ይህ አሁን ባለው ሁኔታ የግብፅና የሱዳን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ሊሸጋገር የሚችልበት ዕድል ሰፊ ነው፡፡

ነገር ግን ግንኙነታቸው ቢሻሻልም እንኳ ሱዳን በዊኪሊክስ የተጠቀሰውን የጦር ሠፈር እስከመፍቀድ ትደርሳለች ወይ የሚለው ግን ከባድ ጥያቄ ነው፡፡ የሱዳን ደኅንነት ተቋም፣ የመከላከያ ኃይሏ፣ ሲቪሉ የብሔራዊ ኮንግሬስ ፓርቲና ፓርላማው የተለያዩ አጀንዳዎችን የሚያራምዱና የተለያዩ የሥልጣን ማዕከሎች (Power Centers) መሆናቸውን ዓለም አቀፉ የግጭት ጥናት ተቋም (International Crisis Group) በተደጋጋሚ የሚገልጸው እውነታ መሆኑ እሙን ነው፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሁሉም የሥልጣን ማዕከሎች ለግብፅ ጦር ሠፈር ለመፍቀድ ተስማምተው ከሆነ ሱዳን በደቡብ ሱዳን መገንጠል ማግስት ጓዟን ጠቅላላ በግብፅ ጉያ ውስጥ እየገባች እንደሆነ የሚያመላክት ይሆናል፡፡

በመረጃው የተጠቀሰው የግብፅ ‹‹ዕቅድ›› ውሎ አድሮ ተግባራዊ የሚሆን ከሆነ ግን ሱዳን በህልውናዋ ላይ እንደፈረደች ይቆጠራል፡፡ በዓባይ ወንዝ አጠቃቀም ላይና በሌሎችም ፖለቲካዊ ጉዳዮች መሠረታዊ የሆኑና ብሔራዊ ጥቅሞቿን የሚመለከቱ ልዩነቶች ከጐረቤቷ ኢትዮጵያ ጋር ሳይኖራት፣ በእንደዚህ ዓይነት ስምምነት ውስጥ ከገባች በፖለቲካ ቋንቋ ራስን እንደማጥፋት (Political Suicide) ቢቆጠር ማጋነን አይሆንም፡፡ እ.ኤ.አ በ1990ዎቹ አጋማሽ አካባቢ የኢትዮጵያ ጦር ከደቡብ ሱዳን አማፂ ጋር በመሆን ወሳኝ ወታደራዊ መሬቶችን በሱዳን ግዛት ውስጥ መቆጠጠሩ የሚዘነጋ አይደለም፡፡ በዚህም ድርጊት የሱዳን መንግሥት ህልውና አደጋ ውስጥ ወድቆ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡

ከሱዳን ጋር መቃቃር የእኛንም የአደጋ ተጋላጭነት እንደሚጨምረው ቢታወቅም፣ በሱዳን በኩል ግን ደቡብ ሱዳን በመገንጠሏና የደቡብ ሱዳን ነፃ አውጪ ሠራዊትም ወደ መንግሥትነት በመለወጡ፣ ቀደም ሲል የነበራት የተጋላጭነት (Vulnerability) መጠን መቀነሱ አይካድም፡፡ ስለሆነም ለዘመናት የዘለቀው የሱዳን ውስጣዊ ደካማ ጐን (Achilles Heels) ተቀርፏል፡፡ ምንም እንኳ የግጭቱ መልክና ቅርፅ ተቀይሮ በሌላ መንገድ ቢቀጥልም ማለት ነው፡፡ ሆኖም ግን የአፍሪካ ቀንድ ፖለቲካ ተለዋዋጭ በመሆኑ ነገ የሚፈጠረውን ለመገመት አስቸጋሪ ነው፡፡

በእርግጥ ሱዳን የተባለውን የጦር ሠፈር የምትፈቅድ ከሆነ የአገሪቱ ስሜት (Siege Mentality) መጨመሩ አይቀርም፡፡ ከደቡብ ሱዳን ጋር በተለያየ ጊዜ ሊነሳ የሚችለው አለመግባባት እንደተጠበቀ ሆኖ የኢትዮጵያ ኩርፊያና ዛቻ ሲጨመርበት የአገሪቱን ሥጋት ያባብሰዋል፡፡ ስለሆነም ሱዳን ከግብፅ የምትጠብቀው ዋነኛው ጉዳይ የጋራ መከላከያ ስምምነት (Mutual Defense Pact) ውስጥ መግባት ይሆናል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ሱዳን ከጐረቤቶቿ ለሚሰነዘርባት ማንኛውም ጥቃት ወይም ወረራ ግብፅ የራሷ ሉዓላዊነት እንደተደፈረ ቆጥራ እንድትከላከልላት የሚያስገድድ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ ሰፊ ስምምነት ግብፅ ትገነባዋለች ለተባለው የጦር ሠፈር ሽፋን መስጠቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ይህ የመሆን ዕድሉ ግን ወደፊት የሚታይ ነው፡፡

ለበርካታ ዓመታት ግጭትና አለመረጋጋት የማይለየው የአፍሪካ ቀንድ እ.ኤ.አ በ2011 እና በያዝነው 2012 በርካታ ሁነቶች አስተናግዷል፡፡ እንደ ኤርትራ ሁሉ በቂ ሕጋዊ ስምምነቶች ሳይጠናቀቁ የተገነጠለችው ደቡብ ሱዳን ከሱድን ጋር ያላት እሰጥ አገባ አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡ በድንበር ላይ የምትገኘው የአቢዬ ግዛትም ለመጪዎቹ ጊዜያት የአለመግባባቱና የግጭቱ ማዕከል ሆኖ እንዳትቀጥል ያለው ሥጋት ከፍተኛ ነው፡፡ በቅርቡ አዲስ አበባ ላይ የተደረሰው ስምምነትም የግዛቷን ጉዳይ ለመፍታት የሚያስችለውን መላ ለማመላከት አላስቻለውም፡፡

ሌላው ክስተት ለዘመናት አይነኬ ተደርጐ ይታሰብ የነበረውን ከግብፅ ዕውቅና ውጭ ዓባይን የመገደብ ፍርኃት የተሰበረው በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ በእርግጥም የኢትዮጵያ መንግሥት ‹‹ታላቁ የህዳሴ ግድብ›› ብሎ የሰየመው ፕሮጀክት ይፋ ሲሆን፣ የታችኛውን ተፋሰስ አገሮች ቀልብ የሳበው ወዲያውኑ ነው፡፡ በዚህ ወቅት ሕዝባዊ አመፅ ግብፅንና የዓረቡን ዓለም እየናጠ የነበረበት ወቅት በመሆኑ ግጥምጥሞሹን አስገራሚ ማድረጉ አልቀረም፡፡ ሕዝባዊ አመፁን ተከትሎም ጥቁር የአፍሪካ ክፍልን ገሸሽ በማድረግ የሚታወቁት የግብፁ መሪ ሆስኒ ሙባረክ ከመንበረ ሥልጣናቸው ተወግደው ዘብጥያ ለመግባት በቅተዋል፡፡

በቅርቡ የተከሰተው ሌላኛው ክስተት ደግሞ የህዳሴው ግድብ መሐንዲስና የአፍሪካ ቀንድ የፖለቲካ ሞተር ዘዋሪ የነበሩት የክቡር አቶ መለስ ዜናዊ ድንገተኛ ሕልፈተ ሕይወት ነው፡፡ በዚህ ክፍለ አኅጉር እስላማዊ አክራሪነትን በግንባር የተፋለሙት አቶ መለስ፣ በአካባቢው የነበራቸውን ስትራቴጂ በቅርብ የሚከታተል ሁሉ አገራቸውን የክፍለ አኅጉሩ ልዕለ ኃይል (Hegemonic Power) ለማድረግ እየጣሩ እነደነበር መረዳት አይሳነውም፡፡
በጠቅላላው ግን የተጠቀሰው መረጃ እውነትነት ወደፊት የሚታይ ቢሆንም፣ ለዚህ ክፍለ አኅጉርና ለግብፅም በዘለቄታዊነት ጠቃሚ የሚሆነው ግን በጋራ ስምምነት ማዕቀፍ ውስጥ መሥራት ብቻ እንደሆነ አያከራክርም፡፡ ጊዜው ኋላቀርና አሮጌ አስተሳሰቦችን በመተው አዳዲስ እውነታዎችን መላመድ የሚያስፈልግበት ወሳኝ ጊዜ ነው፡፡ ሰላም እንሁን፡፡

Advertisements
Categories: Articles
%d bloggers like this: