Home > Articles > ለምን አቶ ኃይለማርያም ፖለቲካዊ ለውጥ ማምጣት አይችሉም?

ለምን አቶ ኃይለማርያም ፖለቲካዊ ለውጥ ማምጣት አይችሉም?

November 10, 2012

በዳንኤል ተፈራ

የባለፈው የኢትዮጵያውያን ዓመት ወደማገባደጃው በድንገተኛ ግዙፍ ክስተቶች የተሞላ ነበር፡፡ እነሆ ያልተገመተው ግዙፍ ክስተት የጠቅላዩ መታመምና ብዙም ሳይቆይ ዜና ዕረፍታቸው መነገሩ ነው፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሞት ተከትሎ እንደተለመደው የቀንዱ ፖለቲካ መጋል ጀመረ፤ ንዝረቱ ከምዕራብ እስከ ምስራቅ ድረስ ተስተጋባ፡፡

በዚሁ ድንገተኛ ዜና የተነሳም የተለያዩ ክስተቶችንና መላምቶችን ለማዳመጥ በቃን፡፡ ከዚህ አንፃርም ኢትዮጵያውያንን በሁለት ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ አንደኛው የኢህአዴግን ስርዓት ተከትሎ የብልፅግና ማማ ላይ የተንሳፈፉት፤ ከስርዓቱ ስር በመሆንና በማጐብደድ ፍርፋሪውን እንደ ጤዛ የሚልሱት፤ ከታጋይነት በፍጥነት ወደ ኢንቨስተርነት የተለወጡት ድንገቴው የፖለቲካ አየር ሌላ ነገር ሳይረብሽ ስርዓቱ እንዲቀጥል ወይም በነበረበት መንገድ ላይ እንዲጓዝ የሚፈልጉት ናቸው፡፡ በሁለተኛ ጎራ የሚመደቡት ደግሞ በነፃነት እጦት በሀገራቸው ላይ እንደ መፃተኛ የሚታዩት፤ የኢኮኖሚው ትሩፋት መሶባቸውን ያልጎበኘው፤ ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ የሚፈልጉ የጠ/ሚኒስትር መለስን ሞት ተከትሎ ከምር ለውጥ እንዲመጣ መሻታቸውን ተመልክተናል፡፡

እጀ ረጃጅሞቹ ምዕራባዊያን በተለይ አሜሪካና እንግሊዝም በምስራቅ አፍሪካ ከፍተኛ የፖለቲካ ጠቀሜታ አላት የሚሏት ኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁናቴ የነሱን ጥቅም ባስጠበቀ መልኩ እንዲቀጥል እንቅልፍ አጥተው እንደሰነበቱ አስተውለናል፡፡ በኢትዮጵያ የሚገኙ የፖለቲካ አታሼዎቻቸውም ያችኑ የማታልቅ የአንገት በላይ ፈገግታቸውን ብልጭ እያደረጉ ጉዳዩን ፈር ለማስያዝ ባጅተዋል፡፡ በረጅም ማንኪያቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው የሚችሉትን ያህል አማስለዋል፡፡

እንዲህም ሆነ፡፡ በፊትም ግምት የተሰጣቸው አቶ ኃ/ማርያም ጠ/ሚኒስትር፤ በርካቶች ከገመቱት ውጭ ድምቡሽቡሽ ያለ መልክ ያላቸውን አቶ ደመቀ መኮንን ም/ጠ/ሚኒስትር በማድረግ ተጠናቀቀ፡፡

ከዚያ በኋላስ? ከዚያ በኋላማ ስርዓቱ እንደነበር ቀጠለ ማለት ነው፡፡ የኢትዮጵያን ፖለቲካ አይናቸው ስር አድርገው የሚከታተሉ በውጭ የሚኖሩና ሀገር ውስጥ ያሉ ልሂቃን እንዲሁም የፖለቲካ ተቺዎች አሁንም ትንታኔያቸውን ቀጠሉ፡፡ ‹‹ሌጋሲ›› የሚለውን ቃል ደጋግመው በመጥራታቸው እንደ ተጨማሪ መገለጫ እየተወሰደባቸው ያለው አቶ ኃ/ማርያም በዓለ-ሲመታቸው ላይ ባሰሙት ንግግር ሳይጨምሩና ሳይከልሱ የመለስን ሌጋሲ እንደሚያስቀጥሉ ተናገሩ፡፡ ንግግሩን ትንሽ ስናፍታታው የኢህአዴጋውያኑን የተንጠለጠለ ልብ ‹‹እፎይ›› ለማሰኘት የታሰበ ይመስላል፡፡ በተጨማሪም የቀድሞዋ ቀዳማዊ እመቤት ወ/ሮ አዜብ መስፍን በባለቤታቸው የቀብር ሽኝት ላይ ‹‹የባለቤቴን ራዕይ ሳይበረዝ ሳይከለስ ከሚቀጥሉት ጐን እቆማለሁ›› ባሉት መሰረትም የተቃኘ ነበር፡፡

አቶ ኃ/ማርያም ዙሪያቸውን ያሰፈሰፉት በተለይ የህወሓትን ሹማምንት ቀልብ ለመግዛትና የኢህአዴጋውያኑን ይሁኝታ በማግኘት ስልጣናቸውን ለማስቀጠል እንደዚያ መናገር ነበረባቸው የሚሉ ወገኖች ‹‹ሃይማኖተኛና ትሁት›› ናቸው የሚባሉትን ጠ/ሚኒስትር ከመተቸት ይልቅ ‹‹ጊዜ እንስጣቸው›› የሚል ሀሳብ ሲያንሸራሽሩ አይተናል፡፡

እነዚህ ወገኖች ለአቶ ኃይለማርያም ‹‹ጊዜ ከሰጠናቸው ለውጥ ሊያመጡ ይችላሉ›› በማለት ጭልጭል የምትል ተስፋ ይዘው መቀጠሉን ይመርጣሉ፡፡ ምክንያታቸው ደግሞ ከኢህአዴግ መሰረታዊ ባህሪ የሚመነጭ ነው፡፡ ኢህአዴግ ጥላውን የማያምን ተጠራጣሪ ድርጅት ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ጠንካራ የደህንነትና የስለላ (በህወሓት የበላይነት የሚመራ) ተቋም አለው፡፡ በተጨማሪም ‹‹የታገልንለት›› የሚል አሮጌ አስተሳሰብ ያላቸውና ‹‹ደም›› እያሰሉ የሚኖሩ ታጋይ ግለሰቦች ጠቅላይ ሚኒስትሩን በቅርብ ርቀት ይከታተላሉ፡፡ ስለዚህ አቶ ኃይለማርያም ይሄን የሚያለዝቡበትና የሚያርቁበት ጊዜ ይሻሉ በማለት ይከራከሩላቸዋል፡፡

ሌሎች በርከት ያሉ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ተከታታዮችና ፀሐፊዎች ደግሞ ‹‹ትሁቱን›› ሰውዬ ‹‹ምንም ለውጥ ማምጣት የማይችሉ፣ አድርግ የተባሉት ከማድረግ በስተቀር አዲስ ውሳኔና አዲስ ለውጥ የማያመጡ›› በማለት የትችት ምታቸውን በቁና ያወርዱባቸዋል፡፡ ከረር ያሉት ተቺዎች ደግሞ ‹‹አሻንጉሊት›› የሚለውን ቃል ለመጠቀም ጥቂት እንኳን አያቅማሙም፡፡

የዚህ ፅሁፍ አቅራቢ ግን ከላይ በቀረቡት ሁለት ግምቶች አይስማማም፡፡ አቶ ኃይለማርያም ምንም ያህል ጊዜ ቢሰጣቸው የኢህአዴግን መስመር ከማስፈፀም በስተቀር ጠብ የሚያደርጉት አዲስ ለውጥ የላቸውም፡፡ ይሄ ማለት ግን ዕድሉ በእጃቸው የለም ማለት አይደለም፡፡ አዲሱ ጠ/ሚኒስትር የኢህአዴግን አብዮታዊ ዴሞክራሲና የልማታዊ መንግስት እሳቤ ለማስፈፀም ያመኑ እንጅ በተለምዶ የፖለቲካ አሻንጉሊት እንደሚባሉት አይነት መሪ አይደሉም ለማለት እደፍራለሁ፡፡ በእኔ እይታ ‹‹አሻንጉሊት›› የሚለው ቃል የራሱ ነገር የሌለው እና በሌሎች የተጫነውን የሚያስፈፅም የሚል ትርጉምን ያዘለ ቃል ነው፡፡ እሳቸው ግን አቶ መለስ የተከሉትን አብዮታዊ ዴሞክራሲ ለማስፈፀም ያመኑ ናቸው፡፡ ለዚህ ነው ጉዳዩ የኃይለማርያም ወይም የወልደማርያም መቀየር አይደለም ብዬ ለመሞገት የምደፍረው፡፡ ጉዳዩ ያለው የተበላሸውን ገዥ ፓርቲ መቀየር ላይ ነው፡፡ ለውጥ የሚመጣውም እንደዚያ ነው፡፡ ለዚህ መከራከሪያ ጥቂት ነጥቦችን እየቆነጠርኩ ማሳየት ይኖርብኛል፡፡ እነሆ 11 ዓመታት ወደ ኋላ ላንሸራታችሁ፡፡

1992 ዓ.ም. ክረምት

በ1992 ዓ.ም. መገባደጃው ላይ የኢትዮጵያ አየር ቀዝቅዟል፡፡ ሰማዩ በሚንቀዋለል ደመና ተሞልቷል፡፡ ቅዝቃዜው የፈጠረው ብርድም የዚያኑ ያህል ጨምሯል፡፡ ኃይለኛ ሙቀትና ግለት ያለው ህወሓት መንደር ብቻ ነበር፡፡ በርግጥም የግለቱ ወላፈን ወደ ሌሎች አጋር ድርጅቶች፤ ኦህዴድ፣ ብአዴንና ደኢህዴን ዘንድም ደርሶ ነበር፡፡

ህወሓትን የለበለበው ግለት ግን ልዩ ነበር፡፡ ነብሳቸውን ይማርና አቶ መለስ ‹‹ቦናፓርቲዝም›› የምትል ጦስ አምጥተው ወደረኛ፣ ወደረኛ የህወሃት ሰዎችን በስራ ባይጠምዱ ኖሮ ህወሓት ፀሐይ እንደነካው በረዶ ሟሙታ ታልቅ ነበር፡፡ ነገር ግን ነገሩ ወዲህ ሆነና፤ ችግራችን ቦናፓርቲዝም ነው? አይ ተንበርካኪነት ነው? በሚል ክርክር ተጠምዱ አቶ መለስም ስራቸውን በፍጥነት በመስራት ‹‹ጋንግሪን ካልተቆረጠ በስተቀር አይድንም›› በሚል የቆየ ብሂላቸው ተጠቅመው አንጋፋ ታጋዮችን አስወገዱ፡፡ የህወሓት ነገርም ለሁለት በመሰንጠቅ ተደመደመ፡፡

በ1992 ዓ.ም. ክረምት ግን ግለቱ አልበረደም፡፡ ኢህአዴግ በከፍተኛ ግምገማ ተጠመደ፡፡ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ስለዚህ ጉዳይ ጠይቄያቸው እንዳጫወቱኝ ‹‹ግምገማው ሃይለኛ ነበር፡፡ ከዚህ በፊትም ተደርጐ አይታወቅም›› ብለውኛል፡፡ እንዴት? የምትል አፍታች ጥያቄም አንስቼ ነበር፡፡ እንዲህ ነው፡-

ግምገማው አቶ መለስን ጨምሮ በፌደራል መንግስት ውስጥ ያሉ ከፍተኛ ካድሬዎችን እና የመንግስት ሰራተኞችን ያካተተ ነበር፡፡ ዓላማውም በአሸናፊነት የወጣውን የህወሓት ክንፍ የበላይነት ማጠናከር ነበር፡፡ በዚያን ወቅት የኢህአዴግና የሻዕቢያ ግንኙነት እንዲሁም ጦርነቱ እንዴት እንደተካሄደም ተገምግሟል፡፡

የአቶ መለስ አቋም የነበረው ‹‹የወደፊት አቅጣጫችንን አስቀምጠን እንገምግም›› የሚል ሲሆን ከህወሓት የተለዩት ስዬ አብርሃ፣ ገብሩ አስራት፣ አለምሰገድና አባይ ፀሐዬ (አሁንም ቀንደኛ የህወሓት ሰው ናቸው) ‹‹ሀገራችን ላይ ያንዣበበው አደጋ ምንድን ነው?›› የሚል እሳት ጥያቄ አንስተው ነበር አሉኝ ዶ/ር ነጋሶ፡፡

ከህወሓት መሰንጠቅ በኋላ ብአዴን ባህርዳር ላይ በአቶ በረከት ስምኦን፣ አዲሱ ለገሰና አቶ ተፈራ ዋልዋ አማካኝነት የተቀመጠ ሲሆን ህወሓት ‹‹ትምክተኛ›› የሚል ስም ይሰጣቸዋል፡፡ ታዲያ ‹‹ቅቤ አልቀቡኝ ለምን ዝም እላለሁ?›› ያለው ብአዴን ‹‹ዝግ በረኞች!›› በማለት መልሱን ሰጥቷል፡፡ በዚህም ህወሓትና ብአዴን ፍጥጫ ላይ ይወድቃሉ፡፡ የኃይል ሚዛኑ እንደሳሳ ያወቀው ብአዴንም የውሸት ሳቀና የፖለቲካ ፕሪሚየር ሊጉን ተቀላቀለ፡፡ የፖለቲካ ተንታኞች በዚያ ቀውጢ ‹‹ህወሓትን ያተረፈው ተመስግኖ የማያውቀው ኦህዴድ ነው›› ይላሉ፡፡ የተጠረገው ተጠረገና ጉዞው ቀጠለ፡፡ ክረምቱም አለፈ፡፡ ‹‹አቶ ኃይለማርያም የፖለቲካ ለውጥ አያመጡም›› ብዬ የምከራከርበት ታሪክ የሚጀምረውም ከዚህ በኋላ ነው፡፡ እነሆኝ፡፡

1993 ዓ.ም. ተሃድሶ

በ1992 በህወሓት መንደር የተፈጠረው ግለት የተለየ አመለካከትና ጥያቄ ያላቸውን ግለሰቦች በመጠራረግ አላበቃም፡፡ ወላፈኑ ወደ 1993 ዓ.ም. ተሸጋግሮ ኢህአዴግና አጋሮቹ በስብሰባና ግምገማ ተወጥረዋል፡፡ አቶ መለስን ጨምሮ ኦህዴድና ደኢህዴን ገምጋሚዎች ሁነዋል፡፡ ከወርሃ ግንቦት ጀምሮም አሁንም ድረስ ‹‹የሁሉ ነገር መሀንዲስ›› እየተባሉ በኢህአዴጋዊያኑ ዘንዳ የሚንቆለጳጵሱት አቶ መለስ ቦናፓርቲዝምን በነካካ እጃቸው ‹‹ተሃድሶ›› የሚል አዲስ መንገድ ይዘው ከተፍ ብለዋል፡፡ ተሃድሶው ማጥመቅና አዳዲስ ውልዶችን መፈልፈል ዋነኛ ዓላማው ሆነ፡፡

የተሃድሶው መሰረታዊ ነጥብ ‹‹ኢትዮጵያን ከ20-30 ዓመት ድረስ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች እንመድባታለን›› የሚል ቀና የሚመስል ሃሳብ የያዘ ሲሆን በውስጡ የኢህአዴግን ተቀናቃኞች በመመንጠር ዘላለማዊ መንግስት ማቋቋም ዋነኛ ዓላማው ነበር፡፡

ኢህአዴግ ‹‹ተሃድሶ ውስጥ ነኝ›› ሲል እና የመሰረታዊ ባህሪ ወይም የቅርፅ ለውጥ ለማድረግ ሲሰናዳ፤ ዴሞክራሲን ገለመሌን መሳቢያ ውስጥ ሲከትና ‹‹መጀመሪያ ዳቦ›› የሚል አዲስ ዜማ ሲያሰናዳ ‹‹ሞዴሎቼ›› ያላቸው ሀገራትም ነበሩ፡፡ እነዚህ ልምዳቸውን እንቀስማለን የተባሉት ሀገሮች ደቡብ ኮሪያ፣ ቻይና፣ ማሌዥያና ታይላንድ የመሳሰሉት ናቸው፡፡

ታዲያ በተሃድሶ ሰበብ አዲስ ዜማ ይዞ ብቅ ያለው ኢህአዴግ /ህወሓት/ ሀገራችን የኢኮኖሚ ለውጥ እንድታመጣ ሰብዓዊ መብትና ነፃነት መቀማት እንዳለባቸው ያወጀው በአደባባይ ነበር፡፡ ለስለስ ባለቋንቋ ‹‹ተግዳሮት›› ተብለው የተቀመጡትን በማስወገድ የልማት ኃይሎችን መሰብሰብ የምትል ቅኔም ተዘርፋለች፡፡ ልማታዊ ባለሀብት፣ ልማታዊ አርሶ አደር፣ ልማታዊ አርቲስት፣ ልማታዊ ሯጭ፣ ልማታዊ ወታደር፣ ልማታዊ ሊስትሮ…. እያሉ ማደራጀትና የማይበረዝና የማይከለስ ነጭ ካፒታሊዝም መከተል የሚል ዓላማም እንዳለው ከህወሓት/ኢህአዴግ መንደር የቃረምነው መረጃ ያመለክታል፡፡

አሁን ጥያቄው ‹‹ይሄን የሚቃወሙትስ?›› የሚለው ነው፡፡ ለዚህም የእነ አቶ መለስ ተሃድሶ መልስ ነበረው፡፡ ‹‹እነዚህማ ፀረ-ልማት፣ ላባቸውን ሳያንጠፈጥፉ ባለሀብት ለመሆን የሚጥሩ ኪራይ ሰብሳቢዎችና ጥገኞች ናቸው›› የሚል፡፡ እነዚህን መሰረታቸውን እንዲያጡ ማድረግ እንደሚገባም ተወስኗል፡፡ ለባለፉት 10 አመታትም የፀረ-ሽብርተኝነት ህጉን የመሰለ የማስፈፀሚያ ገመድና ሌላ ሰበብ ተበጅቶላቸው ‹‹ስርዓቱ በአጉል ጐዳና እየሄደ ነው›› ብለው የተቃወሙት ወደ ወህኒ ወርደዋል፡፡

የልማት ኃይሎች መሪዎችና ‹‹የፀረ-ልማት ኃይሎች መሪዎች›› የሚል ሁለት መደብም ተፈጥሮም ኢህአዴግ ራሱን የልማታዊ ኃይሎች መሪ አድርጐ ሲያስቀምጥ የፀረ-ልማት ኃይሎች የሚለው ምድብ ደግሞ ለሀቀኛ ተቃዋሚዎች ተሰጠ፡ በዚህ መሰረትም ከዚህ በፊት የጐሪጥ ያዩዋቸው የነበሩና ‹‹ስኳር አላሽ›› በሚል ይጠየፏቸው ከነበሩ ባለሀብቶች ጋር ሽርክ ሆኑ፡፡ ለነዚህ ባለሃብቶችም ልማታዊ የሚል ሜዳሊያ ጠለቀላቸው፡፡

‹‹ፀረ-ልማት ኃይሎችን ይመራሉ›› የተባሉ ተቃዋሚዎች ላይ ‹‹እናጠፋቸዋለን!›› የሚል ክፉ አዋጅ የታወጀውም በ1993 የኢህአዴግ ተሃድሶ ወቅት ነው፡፡ ይሄው ዕቅድ ታቅዶና ቡራኬ ተሰጥቶ፣ ጠመቃውም ተካሄዶ፣ ጉዞውም ተጀመረ፡፡ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝም ተሃድሶ ከወለዳቸውና ግራና ቀኝ የዓይን መከለያ እንደተገጠመለት ፈረስ የኢህአዴግን መስመር ተከትለው ከሚፈሱት መካከል ናቸው፡፡ ከዚህ መሰረት በመነሳትም ነው ‹‹ጊዜ ቢሰጣቸውም ለውጥ ሊያመጡ አይችሉም›› የምለው፡፡

አቶ መለስ ዜናዊም ከ1993 እስከ 2004 (በሞት እስከተለዩበት) ‹‹ቆሻሻውን ሁሉ አስወግዶ እሰይ እሰይ ህዳር ታጠነ›› የሚል የተሃድሶ ዜማቸውን እያቀነቀኑ መርተዋል፡፡ ሰብዓዊ መብት፣ ዴሞክራሲ እና መድብለ ፓርቲ የመሳሰሉት ውድ ቃላት ከኢህአዴግ መዝገበ ቃላት ከተፋቁም ከ10 ዓመት በላይ ሆኗቸዋል፡፡

ድንገተኛውን የአቶ መለስን ሞት ተከትሎ ወደ ስልጣን የመጡት አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ‹‹ምንም ለውጥ አይደረግም›› ያሉት እንዲሁ ከመሬት ተነስተው አልነበረም፡፡ በተሃድሶ ሰበብ የተነጠቁ መሰረታዊ መብቶችን ወደ ህዝቡ እንዳይመለሱ ለማድረግና የኢህአዴግን አቅጣጫ ለማስቀጠል ትክክለኛ ሰው ሆነዋል ማለት ነው፡፡ ፓርላማ ቀርበው ባሰሙት ንግግርም ይሄንን አረጋግጠዋል፡፡ ያውም የንግግር ለዛ ሳይቀር ለመኮረጅ ችለዋል፡፡ የአቶ መለስን ‹‹ፈንጅ ወረዳ›› አቶ ኃይለማርያም ‹‹እሳት መንካት›‹› በመለወጥ አቅርበዋል፡፡ የጠ/ሚኒስትር ኃይለማርያም ተግባር ቢኖር አምባገነንነቱን (እሳቸው የመለስ ሌጋሲ ይሉታል) ማስቀጠል ነው፡፡ ስለዚህ ምንም አይነት ጊዜ ቢሰጣቸው፤ ምንም ‹‹ቀና›› ብንላቸው አቶ ኃይለማርያም ፖለቲካዊ ለውጥ ሊያመጡ አይችሉም፡፡ ይሄን ለውጥ ማምጣት የማይችሉት ደግሞ ‹‹አሻንጉሊት›› ስለሆኑ ሳይሆን የስርዓቱ መስመር ከተሃድሶው በኋላ እንደዚያ ስለቀጠለ ነው፡፡

አንዲት ምሳሌ ብቻ ላንሳ፡፡ በ1993 ዓ.ም. አቶ መለስ ከ20-30 ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች እንመደባለን አሉ፡፡ አቶ ኃይለማርያምስ? አቶ ኃይለማርያም ስልጣን ሲይዙ 10 ዓመታት አልፈው ነበርና ይሄን በመቀነስ ‹‹በ10 ዓመት ውስጥ መካከለኛ ገቢ ያላቸውን ሀገሮች እንቀላቀላለን›› አሉ፡፡ የአቶ ኃይለማርያም ስርዓቱን እንዳለ የማስቀጠል ማረጋገጫም ይሄው ነው፡፡ አቶ ኃይለማርያም የተበላሸውን የኢህአዴግ መስመር ለማስቀጠል ባያምኑ ኖሮ ስልጣኑን እሺ ብለው አይቀበሉም ነበር፡፡ ምክንያቱም ምርጫው ወይ ማስቀጠል አሊያም መልቀቅ ነውና፡፡

የተሃድሶው ውልድ-ኃይለማርያም

ከላይ ለመግለፅ እንደሞከርኩት ወይም ለመከራከር እንደከጀልኩት አምባገነንነትን ለማስቀጠል ቃል የገቡት ጠ/ሚ ኃይለማርያም ደሳለኝ አቶ መለስ ያረቀቁት የ1993 ተሃድሶ ፍሬ ናቸው፡፡ እሳቸው አስቀጣይ እንጂ ጊዜ ስለተሰጣቸው ፖለቲካዊ ለውጥ የሚያመጡም፣ አሻንጉሊትም አይደሉም፡፡ እንደውም ለመጀመሪያ ጊዜ የመንግስትን አቋም ለማብራራት ፓርላማ በቀረቡበት ወቅት መለስን መስለው ከመቅረባቸውም ባለፈ ለመብለጥ ተጣጥረዋል፡፡ ይሄ ማለት ግን አቶ ኃይለማርያም ደፈር ካሉ ለውጥ ማምጣት የሚችሉበትና ታሪክ የሚሰሩበት ዕድል ተጠርቅሞ የተዘጋ ነው ማለት አይደለም፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብ የለውጡ ባለቤት ይሆን ዘንድ ሁለት መንገዶች አሉ፡፡ አንደኛው በአቶ ኃይለማርያም እጅ ያለና ምናልባት ከተጠቀሙበት የነፃነት መንገድ ሊሆን የሚችል ሲሆን፤ ይሄም ከኢህአዴግ መዋቅር የሚመነጭ ነው፡፡

ከ1993 ዓ.ም. በፊት የኢህአዴግ ማዕከል ሆኖ የሚያገለግለውና የቀን ተቀን ስራ የሚከውነው የፖሊት ቢሮ ይመራ የነበረው በጣም ጠንካራ በሚባሉ ሰዎች ነበር፡፡ በዓለምሰገድ ገ/አምላክ፣ በረከት ስምኦንና ተወልደ፡፡ እነዚህ ሰዎች የፖሊት ቢሮው የሚያረቀውን አጀንዳ ተጠሪ ለሆነበት ጠ/ሚኒስትርና ም/ጠ/ሚኒስትር በማቅረብ ይሁንታ እንዲያገኝ ያደረጉ ነበር፡፡ ታዲያ ከ1993 ዓ.ም. በፊት የቀድሞው ጠ/ሚ መለስ ገዝፈው እንዳይወጡ ያደረጋቸው ይሄው የፖሊት ቢሮ ጠንካራ መሆን ነበር፡፡ በ1993 ዓ.ም. ዓለምሰገድና ተወልደ ከድርጅቱ ሲወጡ መለስ የፖሊት ቢሮውን በመቆጣጠር ብቸኛ ሆነው የመውጣት እድል አገኙ፡፡

የአቶ ኃይለማርያምም ለውጥ የማምጣት ዕድል የሚመነጨው ከዚህ ነው፡፡ በፖሊት ቢሮው በኩል ያሉ ሰዎች ጥንካሬ እንደበፊቶቹ እንዳልሆነ ይነገራል፡፡ ስለዚህ ፖለቲካዊ ለውጦችን ለማምጣት የፖሊት ቢሮውንና የፖሊት ቢሮው የሚገመግማቸውን አጋር ድርጅቶች መቆጣጠር፣ ከላይ ደግሞ የስራ አስፈፃሚው ላይ ጉልበት በማሳየት ከ1993 ጀምሮ የተበላሸውን የፖለቲካ ጐዳና ማቅናት ይጠበቅባቸዋል፡፡ እነዚህም ተሃድሶው ባመጣው ህግ ሰለባ የሆኑትን ጋዜጠኞችና ፖለቲከኞች መፍታት እንዲሁም ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ሊሰሩባቸው የሚችሉበትን መንገድ ክፍት ማድረግ ናቸው፡፡

ይሄ መሆን ካልቻለ ሁለተኛው መንገድ ግልፅ ነው፡፡ እሱም ስርዓቱን ከናካቴው መለወጥና ስልጣኑን ለህዝብ ማስረከብ፡፡ ይሄ በተቃዋሚ ጐራ የተሰለፉት ኃላፊነት ይሆናል፡፡ ወይም የቤት ስራ፡፡

Advertisements
Categories: Articles