Home > News > ብአዴን ሕወሓትን በባርነት እያገለገለ ያለበትን 32 ዓመት በዓሉን እያከበረ ነው

ብአዴን ሕወሓትን በባርነት እያገለገለ ያለበትን 32 ዓመት በዓሉን እያከበረ ነው

November 30, 2012

(ዘ-ሐበሻ) በአማራ ሕዝብ ስም እየነገደ ነው በሚል እየተተቸ የኖረው የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) የሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ (ሕወሓትን) በታማኝ ባርነት እያገለገለ ያለበትን 32ኛ ዓመት በዓሉን እያከበረ ነው።

“የመለስ ራዕይን አስፈጽማለሁ” የሚለው አነጋገር በኢትዮጵያ ፋሽን በሆነበት በዚህ ወቅት በሕወሓት ባርነት ውስጥ ያለው ብአዴን የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ያወጧቸውንና ኢህአዴግም ያፀደቃቸውን የልማትና የዕድገት ንድፎች በመተግበር ዓላማቸውን ከግብ በማድረስ ራዕያቸውን ማሳካት እንደሚያስፈልግ ለአባላቶቹ በመስበክ ላይ ይገኛል።

በተለይም አቶ መለስ ዜናዊ በሕይወት በነበሩበት ወቅት የተቃጣባቸውን የመፈንቅለ መንግስት በማክሸፍ ታማኝ ባርነታቸውን ያሳዩት የብአዴን ሥራ አስፈፃሚ አባልና ኢህአዴግ የሥልጠና ማዕከል ዋና ዳይሬክተር አቶ አዲሱ ለገሰ በሥልጠና ላይ የሚገኙት የብአዴን ኢህአዴግ ከፍተኛ አመራር አባላትን በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ ሰብስበው “የሰማዕቱን መለስ ዓላማ ለማሳካትና የአገሪቱን ብልፅግና ለማረጋገጥ ጠንክሮ መታገል ያስፈልጋል” በማለት ተናግረዋል። በኢሕአዴግ ውስጥ አቶ መለስን ከዕምነት ሰማ ዕታት እኩል ማየት አዲስ ነገር ባይሆንም ብአዴን ከ32 ዓመታት በኋላም በሕወሓት ባርነት ቀንበር ውስጥ ላለመቆየት አንዳችም ለውጥ አለማሳየቱ የፖለቲካ ታዛቢዎችን እያስተዛዘበ ነው።

አቶ አዲሱ ለገሰ የብአዴን ኢህአዴግ ከፍተኛ አመራር አባላንት በሲቪል ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ በማሰልጠን ላይ መሆናቸውን የጠቁሙት የዘ-ሐበሻ የአዲስ አበባ ዘጋቢዎች ሥልጠናው ከተጀመረ 10 ቀናት ቢያልፉትም እስከ 50 ቀናት ድረስ እንደሚቆይ አስታውቀዋል። የአዲሱ ለገሰ ስልጠና ብአዴንን በሕወሃት ሳንባ እንደተነፈሰ ለቀጣዩ 30 ዓመታት እንዲቆይ የሚያደርግ እንጂ ከባርነት የሚወጣ ድርጅት እንደማያደርገው ታዛቢዎች ይናገራሉ።

ብአዴን በትግሉ ውስጥ የሕወሓት አሽከር ከመሆን ባለፈ በስሙ ለሚነግድለት የአማራ ሕዝብ ያደረገው ነገር እንደሌለ ሲተች ቆይቷል።

Source: Zehabesha.com

Categories: News