Home > News > የዘመናዊት ኢትዮጵያ መሥራች፣ የእምዬ ምኒልክ ሀውልት ከመፍረሱ በፊት፣ የአፍራሹ አገዛዝ መፍረስ አለበት!!

የዘመናዊት ኢትዮጵያ መሥራች፣ የእምዬ ምኒልክ ሀውልት ከመፍረሱ በፊት፣ የአፍራሹ አገዛዝ መፍረስ አለበት!!

December 12, 2012

ሞረሽ

ዲሰምበር 10 ቀን 2012.

ወዳጅም ጠላትም የመሰከረላቸው፣እምዬ ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ፤የዘመናዊት ኢትዮጵያ መሥራች ታላቅ አባት መሆናቸውን ነው፡፡ ዐፄ ምኒልክ ገና ከመወለዳቸው በፊት ታላቅነታቸው የተነገረላቸው ናቸው፡፡ ከጥንት ጀምሮ በምኒልክ ስም የሚነግሥ፣ኢትዮጵያን ታላቅ ያደርጋል የሚል ትንቢት ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ንጉሥ ሣህለሥላሴ ሊነግሱ በተዘጋጁበት ወቅት፣ስመ መንግሥታቸውን ምኒልክ ለማለት አስበው ነበር፡፡ ነገር ግን በዚያን ጊዜ የሰዎችን የወደፊት ዕጣ የመተንበይ ተሰጥዖ ካላቸው ሰዎች አንዱ፣ “ይኸ ስም ለእርሰዎ አይበጅም፤ስሙ ተገቢ የሚሆነው ከልጀዎ ከኃይለ-መለኮት ለሚወለድ ነው” ተብለው በመነገራቸው ስሙን ሳይጠሩበት መቅረታቸው በትውፊት ይነገራል፡፡ የዘመኑ ታሪክ ጸሐፊዎችም ይኸነኑ በመፃሕፍቶቻቸው አስፍረዋል፡፡ የዐፄ ዮሐንስ ለማዳ አንበሣ ከጌታው ከድቶ ለእርሳቸው አድሮ መንገድ መሪያቸውም ሆኗል፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ታሪክ መዛግብት እንደመዘገቡት፣ “ጆሮ ከአያት ያረጃልና” በስሚ ስሚ እንደሰማነውም፣ ምኒልክ በ1848 በዐፄ ቴዎድሮስ ተማርከው መቅደላ በግዞት ለ10 ዓመታት ያህል መቆየታቸው ይታወቃል፡፡ ሰኔ 24 ቀን 1857 ዓ.ም ከባድ ዝናም በመቅደላና በአካባቢው ይጥላል፡፡ በዝናቡ ክብደት የተነሳም፣የአምባው ጠባቂዎች የጥበቃ ቦታቸውን ትተው በአካባቢያቸው በመገኙ ቤቶች ይጠለላሉ፡፡ ከዝናቡ ጋር ተያይዞ የዱር አንበሣ ወደ አንባው ይመጣል፡፡ የአንበሣውን መምጣት የተመለከቱ የአንባው ጠባቂዎች በእሱ ላይ የእሩምታ ተኩስ ይከፍታሉ፡፡ በዚህም በአንባው ውስጥ የተለየ ግርግር ይፈጠራል፡፡ ለረጅም ጊዜ ከእስር የሚያመልጡበትን ሁኔታ ሲያመቻቹ የቆዩት ምኒልክና አብረዋቸው ያሉ የቅርብ ዘመዶቻቸው፣ይኸን ግርግር በመጠቀም ቆቂት በተሰኘችው በር በመውጣት ወይዘሮ ወርቂት ከምትቆጣጠረው ግዛት ይገባሉ፡፡

ወይዘሮ ወርቂት ልጇ በቴዎድሮስ እስርቤት ስለነበር፣ምኒልክን አስራ በመያዝ ምኒልክን መደራደሪያ ለማድረግ በማሰብ እንዲታሰሩ አደረገች፡፡ አከታትላም ለቴዎድሮስ ልጄን የሚፈቱልኝ ከሆነ ምኒልክን አስሬ ላስረክበዎ የሚል መልዕተኛ ላከች፡፡ ሆኖም፣ በምኒልክ ማምለጥ የተናደዱት ቴዎድሮስ በአንባው ታስረው የነበሩትን 41 እስረኞች የወርቂትን ልጅ ጨምሮ ገድለዋቸው ስለነበር፣መልዕክተኞቹ መቅደላ ሳይደርሱ የወርቂት ልጅ መገደሉን በመስማታቸው ተመልሰው የሆነውን ለወርቂት ነገሩ፡፡ ወርቂትም ይኸን እንደሰማች አዝና፣ “ይህ ሰው እግዚአብሔር ያልተለየው ነው፤ገንዘቡንም መልሱ፣እርሱንም በክብር አምጡልኝ አለች፡፡” በመጣላትም ጊዜ፣ “የሸዋ ሰው አውራህ መጥቷልና ደስ ይበልህ!” ብላ አዋጅ አስነግራ በአጃቢ ወደ አሊቡኮ እንደላከቻቸው ይታወቃል፡፡

ምኒልክ ሸዋ ገብተው ተቀናቃኞቻቸውን አስገብረው “ ምኒልክ ንጉሠ ነገሥት ዘኢትዮጵያ ዘአዳል ወጋላ” የሚል ማኅተም አሠርተው የመሐልና ደቡብ ኢትዮጵያ አዛዥ የመሆናቸው ጉዳይ፣ለዐፄ ዮሐንስ ሥልጣን ምቹ ሆኖ አልታየም፡፡ በመሆኑም ዐፄ ዮሐንስ ምኒልክን ለማስገበር በ1870 ወደ ሸዋ ዘመቱ፡፡ የምኒልክ ሠራዊት በብዙ መልኩ ከዮሐንስ ጋር መሳ አለመሆኑን በማየት፣ ምኒልክ ያለአንዳች ጦርነት ከዮሐንስ ጋር ልቼ ላይ በመገናኘት፣ምኒልክ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት የሚለውን ማዕረግ ሊተው፣የሸዋ ንጉሥ እንዲባሉ፣ ዮሐንስ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ሊሆኑና ምኒልክ ለዮሐንስ ሊገብሩ ስምምነት አደረጉ፡፡ ከስምምነቱ በኋላ ዐፄ ዮሐንስ መጋቢት 25 ቀን 1870 ከልቼ ተነስተው ወደ ደራ ሲጓዙ ያስከተሉት ለማዳ አንበሣ አልንቀሳቀስም ብሎ ይተኛል፡፡ የአንበሣው አሰልጣኝ ጉዳዩን ለዮሐንስ ይነግራል፡፡ እርሳቸውም “አሞት ይሆናል ተወው” በማለት ሠራዊታቸውን መርተው ወደፊት ይሄዳሉ፡፡ ከዐፄ ዮሐንስ ጋር አልሄድም ያለው አንበሣ፣ከተኛበት ተነስቶ ከምኒልክ ሠራዊት ጋር በመቀላቀል ከንጉሥ ምኒልክ ፊት ፊት መጓዙ ታውቋል፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ሲጤኑ፣ ለምኒልክ ከእስር መውጣት ምክንያት የሆነው ዝናብና የዱር አንበሳ፣ከዮሐንስ ቀጥሎ የኢትዮጵያ መሪ ሊሆኑ የሚችሉት ምኒልክ መሆናቸውን የራሳቸው የዐፄ ዮሐንስ ለማዳ አንበሣ ወዶ መግባቱ፣ምኒልክ እንኳን ሰው አንበሣው የሰገደላቸው ናቸው ቢባል ውሸት የሚሆነው ምኑ ላይ ነው ?

ከዚህ በኋላ ምኒልክ በግራኝ ጦርነትና በኦሮሞ ፍልሰት ምክንያት ኢትዮጵያዊ የአንድነት ስሜቱ ላልቶና ወይቦ የነበረውን የደቡብ፣ የምዕራብና የምሥራቅ ኢትዮጵያን ልዩ ልዩ ነገዶችና ጎሣዎች ፣እሽ ያለውን ያባቱን አገር እየፈቀዱ በሰላም፣እምቢ ያለውን በኃይል እያንበረከኩ የጥንት የአባቶቻቸውን አገር መልሰው ማዋሀዳቸው ይታወቃል፡፡

በ1880 ላይ ዐፄ ዮሐንስ መተማ ላይ ከድርቡሾች ጋር ባደረጉት ጦርነት ሕይዎታቸው ሲያልፍ፣ ምኒልክ የኢትዮጵያ ብቸኛ ኃያል ስለነበሩ፣ያለብዙ ግርግር የፖለቲካ ሥልጣን ባለቤት በመሆን፣ኢትዮጵያን ወደ ዘመናዊነት ያሸጋገሩ ብቻ ሳይሆኑ፣የአውሮፓን ቅኝ ገዥ ኃይል በ1896 ዐድዋ ላይ ድል በመንሳት የቅኝ ገዥዎችን ቅስም የሰበሩ ብቸኛው መሪ ናቸው፡፡በዚህም አድራጎታቸው፣ኢትዮጵያ የአፍሪካ የነፃነት ቀንዲል እንድትባል ያስቻሉ ብቻ ሳይሆኑ፣ የዘመኑ ኃያላን መንግሥታት የነበሩት፣እንግሊዝ፣ፈረንሣይ፣አሜሪካ፣ ጣሊያንና ቤልጂየም በአፍሪካ ብቸኛዋ ነፃ አገርና መንግሥት መሆኗን አምነው ተቀብለው የዲፕሎማሲ ግንኙነት እንዲመሠረት ያደረጉ ናቸው፡፡ በዚህም የኢትዮጵያን ወርድና ቁመት ከኃያላኑ ጋር ተረደራድረው የወሰኑ ናቸው፡፡

ይህም ብቻ አይደለም፡፡ ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ ዘመናዊ ትምህርት፣ኤሌክትሪክ፣የቧንቧ ውኃ፣ባቡር፣አውቶሞቢል፣ማተሚያቤት፣ባንክ፣ሆቴል፣ስልክ፣ፖስታ፣ሆስፒታል፣ፋርማሲ፣ጋዜጣ፣ፎቶግራፍ፣ የባቡር ሐዲድና ጥሪጊያ የመኪና መንገድ፣የጽሕፈት መኪና፣ የእህል ወፍጮ፣ ከሁሉም በላይ ዘመናዊ የመንግሥት ቢሮክራሲን ለመጀመሪያ ጊዜ ያደራጁ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ የመጀመሪያው የመኪና አሽከርካሪ እርሳቸው መሆናቸውን ስንቶቻችን እናውቅ ይሆን? ምኒልክ በዚያን ጊዜ ቀርቶ ዛሬ እንኳን ለብዙዎች አዕምሮ እንግዳ የሆነውን በሰውልጆችና በሃይማኖቶች ዕኩልነት በጽኑ የሚያምኑ ሰብአዊ መሪ ስለነበሩ ሕዝባቸው “ እምዬ” ምኒልክ ሲል ይጠራቸው እንደነበር ይታወቃል፡፡ምኒልክ ደግ፣ ርኅሩኅ፣ ቸር፣አስተዋይና አርቆ ተመልካች የነበሩ መሪ ብቻ ሳይሆኑ፣ የአባትነት መንፈስ በላያቸው ላይ ያረበበባቸው እንደነበሩ ያዩዋቸው ሁሉ የመሰከሩላቸው ናቸው፡፡

ዐፄ ምኒልክ ከማንም በፊት በሰው ልጆችና በሃይማኖቶች ዕኩልነት የሚያምኑ እንደነበሩ በዘመነ መንግሥታቸው የተጻጻፏቸው ደብዳቤዎች ያረጋግጣሉ፡፡ የካቲት 8 ቀን 1902 ዓ.ም ለጅማው አባጅፋር እንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፤

ይድረስ ካባ ጅፋር፣

ይህንን የደንብ ወረቀት ጽፈንልሃል፤

ከጃንጃሮ ወዳንተ አገር የመጣውን ጋላ እንግዲህ ከእጄ ከገባልኝ ብለህ ጭቡ አድርገህ ባርያዬ ነህና አንተንም ልበድልህ፣ልጅህንም አምጣና እንደከብት ልሽጠው ፣ልለውጠው አትበል፡፡ይህን ያህል ዘመን አባቶቻቸው ከአባቶችህ፣ልጆቹ ካንተ ጋር አብረው ኑረው ባሪያ ሊባሉ አይገባም፡፡ባደባባይም ባርያዬ ነው እያልክ አትሟገት፡፡የሰው ባርያ የለውም፡፡ሁላችንም የእግዚአብሔር ባርያዎች ነን፡፡እግዚአብሔር መርጦ፣ከሰው አልቆ ሲያስገዛ ጊዜ በሰው መጨከን አይገባም፡፡ለሰው ቢያዝኑ ዕድሜ ይሰጣል፡፡

…..ደግሞ እንደወደደበት እተመኘው ቦታ ላይ ይቀመጥ እንጂ፣ካንተ አገር ተነስቶ ወደ ጃንጃሮ ቢሄድ፣ወደ ሌላም ወደ ወደደው አገር ቢሄድ የኔ ዜጋ ነው ብለህ ልትይዝ አይገባም፡፡የጃንጃሮው ሰው ፣የሌላም አገር ሰው አንተን ወዶ ወደ አንተ አገር ቢገባ፣የጃንጃሮም ገዥ ሌላውም ገዥ ሁሉ የኔ ዜጋ ነው ብሎ አይያዝ፡፡ ደሀው እወደደው እተመቸው ቦታ ይደር፡፡(ጳውሎስ ኞኞ 1984፣33-34)

በሌላ በኩል ይህን ደብዳቤ ለአባ ጅፋር ከመጻፋቸው ሁለት ዓመት ቀደም ብሎ የካቲት 29 ቀን 1900 ዓ፣ም የባሪያን ንግድ የሚያስቀር አዋጅ አውጀው ነበር፡፡ የአዋጁም ፍሬ ነገር እንዲህ የሚል ነው፡፡

…..የባሪያ ነገር አትሽጥ፣አትግዛ ብየ ከዚህ ቀደም በአዋጅ አስከልክየ ነበር፡፡ አንተ ግን ውስጥ ውስጡን መሸጥክን ፣መግዛትህን የማትተው ሆንክ፡፡ይልቁንም በዳር በዳር ያለው ሚስቱንም ልጁንም ይሸጥ ዠመር ማለት ሰማሁ፡፡አሁንም በዳር አገር በሌላም አገር ቢሆን ባሪያ መሸጥና መግዛት ተወኝ፡፡ እንግዲህ ባሪያ ስትሸጥ፣ስትገዛ የተገኘህ ሰው እስከ ዘመድህ ድረስ እያሰርሁ ሥራ ለሚሠራ ሰው እሰጥሃለሁ፡፡(እንደላኛው)

ዐፄ ምኒልክ በሰዎች ዕኩልነት የጸና እምነት የነበራቸው መሆኑ የሚታየው ባርነትን በመከልከላቸው ብቻ ሳይሆን፣ “ ሁላችንም የእግዚአብሔር ባሮች ነን” ሲሉ ያሰፈሩት ቃል ሰው በሰው ላይ ጌታ ሊሆን እንደማይችል፣ሁሉም በአንድ አምላክ የተፈጠረ፣ ባርነቱ ለፈጣሪው እንጂ፣ለእኩያ ተፈጣሪው እንዳልሆነ የሚያስገነዝብ ነው፡፡ ምኒልክ ከሰዎች ዕኩልነት አልፎ በሃይማኖቶች ዕኩልነት የሚያምኑና ይኸንም በሥልጣን ዘመናቸው ተግባራዊ ያደረጉ እንደነበሩ በግልጽ ይታወቃል፡፡ ዊልቤ የተባለ ተጓዥ ሩዶልፍ ሐይቅ ድረስ ተጉዞ በ1893 ባሳተመው መጽሐፉ፣ “…… በጠረፍ ያሉ ሰዎች ምኒልክ ጥሩ ሰው እንደሆነ ያውቃሉ፡፡ምኒልክ ሁሉም ሰው በሃይማኖቱ ይደር ስላለና በሕዝቡም መሀል አድሎና የኃይል ሥራ ስለማይሠራ ይወዱታል” ሲል በአካል ያየውንና ተጠቃሚዎቹ የነገሩትን ጽፏል፡፡ የእነዚህ ድምር ውጤት ነው ምኒልክን እምዬ ያሰኛቸው፡፡ዳግማዊ ዐፄ ምኒልክ በነዚህና መሰል ሥራዎቻቸው ስማቸው በየትኛውም ዓለም ጎልቶ እንዲነገርና እንዲታወቅ ሆነ፡፡ በዚህም የተነሳ በበርካታዎቹ የአፍሪካ መዲዎች በስማቸው መንገዶች ተሰይመዋል፡፡

“የጓሮ ጠበል የልጥ መንከሪያ ይሆናል” እንዲሉ ሆኖ፣ በዚያን ዘመን እንኳን የአውሮፓን ቅኝ ገዥ ኃይል በጦር ኃይል ድል ማድረግ ቀርቶ፣ ለመግጠም ማሰብ የማይቻል በነበረበት ወቅት ፣ቅኝ ገዥውን ኃይል ፊት ለፊት ገጥመው ድል የነሱና ከኢትዮጵያ አልፈው ለአፍሪካ የነፃነት ብርሃን ያበሩ የጀግኖች ጀግና፣የኢትዮጵያን ነባር አንድነት በኢኮኖሚ በተሳሰረ ዘመናዊ የአደረጃጀት መሠረት የጣሉ፣ተፈርተው ሳይሆን ፣ተወደውና ተፈቅረው ተከባሪ የነበሩ የዘመናዊት ኢትዮጵያ መሥራች አባት፣ በታሪክ ማስታወሻነት በስማቸው የሚጠሩ ተቋሞች አንድ ሆስፒታል፣አንድ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤትና አራዳ ጊዮርጊስ ፊት ለፊት በልጃቸው በንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ምኒልክ የተሠራላቸው ሀውልት ነው፡፡ የሀውልቱን ታሪክ የተከታተለ ማንም ሰው እንደሚያውቀው፣ሀውልቱ የተሠራው ጀርመን ነው፡፡ የተሠራበት ቁስ ነሐስ ሲሆን ፣ሠሪው ሐርቲል የተባለ ጀርመናዊ ነው፡፡ ሀውልቱ ተመርቆ የተከፈተው ንግሥት ዘውዲቱ ከሞቱ አንድ ዓመት በኋላ፣ ጥቅምት 22 ቀን 1923 ዓ.ም ነው፡፡ ተመርቆ የተከፈተውም በአልጋወራሽ ተፈሪ መኮንን ንግሥ በአል ዋዜማ ነው፡፡

የኢትዮጵያን ነፃነት ተጋድሎ ታሪክ በሚገባ የሚገነዘብ ሰው፣የምኒልክ ሀውልት መሀል አዲስ አበባ ላይ መቆም ማለት፣የኢትዮጵያና የአፍሪካ ኩራት፣የኢትዮጵያ ሕዝብ ጀግንነትና የዐፄ ምኒልክ የአመራር ብቃት ጉልህ ማሳያ፣ በአንፃሩ የጣሊያን ሽንፈትና ውርደት፣የቅኝ ገዥ ኃይሎች በጥቁር ተሸናፊ የሆኑበትን አፍ አውጥቶ የሚናገር በመሆኑ፣ፀረ-ኢትዮጵዮጵያ ኃይሎችና ምዕራባውያን ይህን ማየት ፈጽሞ አይሹም፡፡ በመሆኑም ጣሊያን የዐድዋን ሽፈት ለመበቀል 40 ዓመት ሠፊ ዝግጅት አድርጎ፣ ሁለንተናዊ ኃይሉን አደራጅቶ ፣በ1928 ዓለም በከለከለውና ባወገዘው ሙስታርድ ጋሥ ጭምር ካየር በመጠቀም አዲስ አበባን ሲቆጣጠር የመጀመሪያ የጥፋት ዒላማው ያደረገው የእምዬ ምኒልክን ሀውልት ነበር፡፡ በመሆኑም ሐምሌ 4 ቀን 1928 ሀውልቱን አንስቶ በጥልቅ ጉድጓድ ውስጥ ቀበረው፡፡ ኒዮርክስ ታይምስና ኢትዮጵያ ኒውስ የተሰኘ ጋዜጣ እ.ኤ.አ የካቲት 13 ቀን 1933 ባወጣው ዕትሙ ስለምኒልክ ሀውልት አቀባበር እንዲህ ሲል ዘግቧል፡፡ “….ኢጣሊያኖች የምኒልክን ሀውልት ሲሰርቁ የተመለከተ ትንሽ ልጅ ጮኾ አለቀሰ፡፡ ሕፃኑ ለምን እንደሚያለቅስ ጣሊያኖቹ ሲጠይቁት፣የንጉሤን ምስል ስለወሰዳችሁ ነው አላቸው፡፡ እነርሱም ከሞሶሎኒ ሌላ ንጉሥ እንደሌለ ነግረውና ገርፈው አባረሩት፡፡”(ጳውሎስ ኞኞ 1984፣) ልጁም በደረሰበት ድብደባና የኅሊና ስብራት ታሞ መተኛቱ ተዘግቧል፡፡

የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ፣የኢትዮጵያ አንድነት አስጠባቂ ሁነኛ መሪ ባጣች ጊዜ ሁሉ የኢትዮጵያዊነት መገለጫ የሆኑ የወል ዕሴቶች በፀረ,ኢትዮጵያ ኃይሎች ሲቃጠሉ፣ሲዘረፉና ሲወድሙ መኖራቸው ግልጽ ነው፡፡ ይህ ተከታታይነት ዛሬም ባለማቋረጡ፣የፋሽስቱ ሞሶሎኒ ርዕዮት አራማጆች የምኒልክን ሀውልት ለሁለተኛ ጊዜ ሊቀብሩት ዝግጅታቸውን አጠናቀዋል፡፡ በቀደመው ጊዜ ሕፃኑ ልጅ የንጉሤን ምስል አትስረቁብኝ ብሎ አለቀሰ፤በዚህ አድራጎቱም ፋሽስቶቹ መቱት፤ንጉሥህ ሞሶሎኒ ነው አሉት፤ በዚህም ተናዶ ታመመ፤ተኛ፡፡ ዛሬ ለምኒልክ ሀውልት መፍረስ ማን ይጠይቅ ይሆን / ማንስ ያለቅስ ይሆን ? ማንስ ይታመም ይሆን?

ጣሊያን የእምዬ ምኒልክን ሀውልት አርቆ የቀበረው የዐድዋ ሽንፈቱን ለመበቀል እንደሆነ ለማንም ግልጽ ነው፡፡ የዛሬዎቹ ወያኔዎች ሀውልቱን ለማፍረስ ቆርጠው የተነሱትም በምኒልክ ላይ የሚከተሉት ቂሞች ስላሏቸው ነው፡፡

  1. ወያኔዎች ምኒልክ ዐማራ ናቸው ብለው ስለሚያምኑ፣ዐማራ ደግሞ የትግሬ ቀንደኛ ጠላት ስለሆነ መጥፋት አለበት ብለው ዘራቸውን በፀረ-ዐማራ በወታደር አደረጃጃት አደራጅተው ለሥልጣን የበቁ በመሆኑ፣ የዐማራው ምኒልክ ሀውልት በሚገዙት አገር መዲና ላይ ቆሞ መታየት የተነሱበትን የፀረ-ዐማራ ትግል የሚሽርባቸው በመሆኑ ሀውልቱ በልማት ስም እንዲፈርስ ወስነዋል፡፡
  2. የዘራችን የዐፄ ዮሐንስን ሥልጣን የቀሙ ምኒልክ በመሆናቸው፣ ምኒልክ በወያኔ/ትግሬዎች ዘንድ የትግሬ አውራ ጣላት ተደርገው የተወሰዱ በመሆኑ፣ጠላታችን ነው የሚሉት የምኒልክ ሀውልት እንዲኖር ባለመፈለግ እንዲፈርስ ወስነዋል፡፡
  3. ምኒልክ የኢትዮጵያን አንድነት በኃይል ያሰገኙ ፣የብዙ ነገዶችንና ጎሳዎችን ያለፈቃዳቸው ያስገበሩ ስለሆነ፣ የነገድና ጎሳዎች ጠላት ናቸው ብለው ወያኔዎች አጥብቀው ስለሚያምኑ፣ዛሬ አገሪቱ በቋንቋ ተሸንሽና በወያኔ የበላይነት በምትገዛበት ዘመን የምኒልክ ሀውልት የቆሙለት ዓላማ ተፃራሪ በመሆኑ እንዲፈርስ ወስነዋል፡፡
  4. ወያኔ አገሪቱን እየገዛ ያለው ተወዶ ሳይሆን፣ በኃይል መሆኑ ምርጫ 97 ልዩ ትምህርትና ተመክሮ ሰጥቶን አልፏል፡፡የኃይል ምንጩ ደግሞ ምዕራባዉያን መንግሥታት መሆናቸው ይታወቃል፡፡ ምዕራባውያኑ ደግሞ ጠንካራ ኢትዮጵያን አይፈልጉም፡፡ ምኒልክ የጠንካራ ኢትዮጵያ ምስል ከመሆናቸውም በላይ፣የነጮች ቅስም ሰባሪ በመሆናቸው ይወዷቸዋል ተብሎ አይገመትም፡፡ በዚህም የተነሳ ሀውልታቸው ቢፈርስ እንደሚደሰቱ ይገመታል፡፡
  5. ከሁሉም በላይ ወያኔ የኢትዮጵያን ነባር ታሪክና አንድነት ሽረን በአዲስ መልክ፣በወያኔ አምሳል መመሥረት አለብን፣እየመሠረትናትም ነው ብለው ስለሚያምኑ፣ነባር ታሪኮችን አፍርሶ ወያኔ ሠራሽ በሆኑ ለመተካት ካላቸው አቋም የተነሳ በልማት ስም ሀውልቱ እንዲፈርስ ወስነዋል፡፡
  6. የምኒልክን ሀውልት ለማፍረስ ሌላው ምክንያት፣ ደጋግመው የወያኔ ባለሥልጣኖች እንደተናገሩትና እንደጻፉት ዐማራና ኦርቶድክስ ሃይማኖትን ላይመለስ ገድለን ቀብረነዋል ማለታቸው አይዘነጋም፡፡ ይህ ከሆነ ቁሞ ያስቸገራቸው የምኒልክ ሀውልት በመሆኑ እርሱንም ለመቅበር የተዘጋጁ መሆኑን መገንዘብ አይገድም፡፡

እነዚህ ምክንያቶች ዕውነት ባይሆኑማ ኖሮ፣በርካታ አማራጮች እያሉ፣የባቡር ሐዲድ መሥመሩን ዲዛን የሠሩ ሙያተኞችም ልዩ ልዩ አማራጮችን ሰጥተዋቸው እያለ፣ በወጭ ምክንያት ሀውልቱ መፍረስ አለበት ከሚል ውሣኔ አይደርሱም ነበር፡፡

ወያኔ የጣሊያን ጉዳይ አስፈጻሚና ራሳቸው ደጋግመው እንደነገሩንም፣ፀረ-ዐማራና ኦርቶዶክስ ሃይማኖት መሆናቸው ሌላው ማሳያ ጭብጥ፣የፋሽስት ጠር፣ለሃይማኖታቸውና ለአገራቸው ነፃነት ሲሉ፣ሕዝቡን ብቻ ሳይሆን፣ምድሪቱ ጭምር ለጣሊያን እንዳይገዙ ገዝተው በግፍ በመትረየስ ተደብድበው የተገደሉት የሰማዕቱ አቡነ ጴጥሮስ ሀውልትም ዐማራና ፀረ‹ቅኝ አገዛዝ በመሆናቸው ብቻ ፣ለመታሰቢያነት የቆመላቸው ሀውልት ልክ እንደ ምኒልክ ሀውልት ሁሉ በልማት ስም እንዲፈርስ ተወስኖበታል፡፡

እነዚህና መሰል የወያኔ ተግባሮች ባንድነት ተጠቃለው ሲታዩ፣ወያኔ የዐማራን ዘሩን ብቻ ሳይሆን ታሪኩንና የኢትዮጵያዊነት የወል መገላጫ የሆኑ ዕሴቶችን፣ተቋሞችን፣አሠራሮችን ፣ግንኙነቶችን ወዘተ ለማጥፋት ሠፊ ዘመቻ የከፈተ መሆኑን የሚያረጋግጡ ናቸው፡፡ ሞረሽ ወገኔ የዐማራ ድርጅት ይህን ዐማራንና ኢትዮጵያዊነትን ለማጥፋት ወያኔ የተያያዘውን ዘመቻ አጥብቆ ይቃወማል፡፡ በመሆኑም በኢትዮጵያ አንድነትና በኢትዮጵያዊነት የምናምን ሁሉ ፣በተለይ ደግሞ ዘርህና ታሪክህ እንዲጠፋ መጠነ ሠፊ ዘመቻ የተከፈተብህ የነገደ ዐማራ ማኅበረሰብ እነዚህ የማንነትህና የታሪክህ ፈርጥ የሆኑት ሀውልቶች ከመፍረሳቸው በፊት የአፍራሹን አገዛዝ ለማፍረስ በየትኛውም አቅጣጫ መንቀሳቀስ ይጠበቅብሃል፡፡

ጣሊያን የምኒልክን ሀውልት ሲያፈርስ የንጉሤን ምስል ለምን ታፈርሳላችሁ ብሎ ያለቀሰው ሕፃን ፣ዛሬም እኛ የመንፈሣዊና ሥጋዊ መሪዎቻችንና አባቶቻችን ሀውልት አይፈርስም በማለት ከማልቀስ ባሻገር እስቲ! ልንል ይገባል፡፡

ከተባበርን ድል የኛ መሆኑ እርግጥ ነውና እንተባበር!

MORESH – Amara Union

1629 K Street NW, Suite 300

Washington DC, 20006

Tel. 202-600-7777

e-mail: moreshamaraunion@hotmail.

Advertisements
Categories: News
%d bloggers like this: