Home > Articles > ሁለተኛው የኢህአዴግ መንግስት

ሁለተኛው የኢህአዴግ መንግስት

December 23, 2012

ሁለተኛው የኢህአዴግ መንግስት

አስራት አብርሃም

የሰለሜን ጭፈራ በዓይነ ህሊናችሁ ተመልከቱ። ፊተኛው ወይም መሪው አለንጋውን ይዞ ከኋላው ያሉትን በአለንጋው ሾጥ ሾጥ እያደረገ ጭፈራውን ያስነካዋል። አሁን ደግሞ ሁለተኛው የኢህአዴግ መንግስት የስልጣን ተዋረድ እንመልከትና በሰለሜ ጭፈራ መልክ እንደርድረው። አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ ከፊት ይሆናሉ። ባዶ እጃቸው ናቸው። አለንጋው የያዘው ሰው ደግሞ ከኋላ ይሆናል፤ ይህ ባለ አለንጋ በአንድ በኩል የህወሀት አርማና የመለስ ምስል ያለው ባርኔጣ ያደረገ ነው፤ በሌላ በኩል ደግሞ በቀኙ ወታደራዊ ኮከብ፣ በግራው “ደህንነት” የሚል ፅሁፍ ያለው ምልክት አድርጓል። ይህ ኢህአዴግ ሪሚክስ ያደረገው የሰለሜ ጭፈራ ነው። አሁን ሰልፉን በደንብ ተመልከቱ ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ ደመቀ መኮነን፣ ሙክታር ከድር፣ ደብረ ፅዮን ገብረሚካኤል፣ ቴዎድሮስ አድሐኖም፣ በረከት ስምኦን፣ አባይ ፀሐዬ፣ አዲሱ ለገሰ፣ መጨረሻ ላይ የህወሀት አርማና የመለስ ምስል ያለው ባርኔጣ ያደረገው፤ ባለ ወታደራዊው ኮከብና ባለ ደህንነት ምልክቱ ሰውዬ ከነአለንጋው ይሆናል ማለት ነው። ይህ ዓይነቱ ጭፈራ ለኢህአዴጎች የተመቻቸው ይመስላል። ህዝቡ ይመቸው አይመቸው ገና ነው በደንብ አልታወቀም። ተቃዋሚዎች ግን በእርግጠኝነት ይሄ ነገር አልተመቻቸውም። ምክንያቱምኢህአዴግ በራሱ ጊዜ ተፈረካክሶ ይወድቃል ብለው እንደሁልጊዜው ሲጠብቁ በአንፃሩ እየተጠናከረ በማየታቸው ደስተኛ አይደሉም።

እንግዲህ ኢህአዴግ ሕገ መንግስቱን አሽቀንጥሮ በመጣል ሶስት ምክትል ጠቅላይ ሚንስትሮች እንዲኖሩት ተደርጓል። የአቶ ኃይለማርያም መንግስት ግን በስንት ባላ ነው የሚቆመው! ይህ በዋነኝነት የህወሀት ቀጥሎ ደግሞ የኦሆዴድ ጥያቄ የመለሰ ሆኗል። አቶ መኮነን ደመቀ ከብቸኛ አልጋዋራሽነት ወደ ምንም ወርዷል። ስለዚህ ብአዴን ልክህን እወቅ የተባለ ይመስላል፤ ብአዴንም ይሄ ነገር በፀጋ የተቀበለው ነው የሚመስለው ምክንያቱም ብአዴን ወደፊት መጣ ቀረ ከኋላው ሊያሰልፈው የሚችል ኃይል ያን ያህል ነው። ይህ የሆነበት ምክንያት ደግሞ እወክለዋለሁ የሚለውን ህዝብ መንፈስ የሌለው በመሆኑ ነው።

ህወሀት ካኮረፈ ነው ችግር የሚሆነው ጠመንጃውን በእጁ የያዘ ኃይል አኮረፈ ማለት መልዕክቱ ግልፅ ነው። የኦሆዴድ ማኩረፍም ለኦነግና ለግንቦት ሰባት የሚጠቅምን፣ የመግቢያ በር እንዲያገኙ ማድርግ ነው። ሌላው የአቶ በረከት ስምኦን ወደ ፈንጂ ወረዳ መንገባት እነ አቦይ ስብሀት ኃይል እንዲያገኙ አድርጓል። ለዘመዶቹ ሄዶ አይዟችሁ የመሬቱን ነገር… የሚል ተስፋ ሰጥቷል የሚል ፕሮፓጋንዳ እንዲነዛባቸው ሆኗል።

ይህም

1ኛ ባድሜ የእኛ አይደለችም በማለት

2ኛ የአሁኑ የኢትዮጵያ ትውልድ ተቀይሯል። እኛ አዲስ አበባ ስንገባ የአስር ዓመት የነበረው አሁን ሰላሳ አንድ አመቱ ነው ይሄ ትውልድ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር እንደነበረች ላያውቅ ይችላል። ስለዚህ አሰብ ምናምን የሚሉትን የሚሰማቸው የለም(እዚህ ላይ የእኔ ትውልድ ለሆነው ኢትዮጵያዊ ወጣት አንድ ጥያቄ አሉኝ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር እንደነበረች የማታውቁ እስኪ እጃችሁን አውጡ! የአቶ በረከት ልጆች ይሄን የማያውቁ ከሆኑ አላውቅም)

3ኛ ኤርትራውያን ከኢትዮጵያ እንዲባረሩ ያደረጉት እን ተወልደ፣ እነ ግበሩ አስራት እነ ስዬ አብርሃ ናችው። እኔና መለስ ይሄ ነገር አግባብ አይደለም ብለን ተቃውመን ነበር። ይሄ የአቶ በረከት ኑዛዜ ህወሀትን ከመናቅ ጋር ነው የተቆጠረው። ስለዚህ ሶስት ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር የሚባል ነገር የለም ባሉ ማግስት ሶስት ጠቅላይ ሚንስተር በመሾም ልካቸውን እንዲያውቁ ተደርጓል። በነገራችን ላይ የቀድመዋ ቀዳማዊት እመቤትስ የት ጠፉ! ዋናውን ስልጣን ሲመኙ ከትፍራፊውም ሳይሆኑ ቀሩ አይደል። እነ ስብሀት ቡድን አልቻሉቱም ማለት ነው! ልጅ ቢሮጥ አባቱን አይቀድምም ነው የሚለው ተረቱ! አቶ ስብሀት ነጋ የኢትዮጵያን ልኡክ መርተው ጀርመን የሄዱ ጊዜ ነው ምልክቱ የታየው።የብዙ ዓመት ልምድ የሚጠቅመው ለዚህ ጊዜ ነው።

እንግዲህ ባለፈው ጊዜ እንዳልኩት ሁለተኛው የኢህአዴግ መንግስት ከአቶ መለስ መሞት በኋላ ስርዓቱን እንዴት ማስቀጠል እንደሚችል ጥረት እያደረገ ነው። የመጀመሪው ሙከራ አቶ ኃይለማርያም ከፊት፣ ምክትል ደግሞ ከብአዴን አቶ ደመቀ በማድረግ ነበር ስርዓቱን ለማስቀጠል ተሞክሮ የነበረው። ይህ ያስነሳው አቧራ ግን በቀላሉ የሚታለፍ አልሆነም። የዚህ ምክንያት አንድም ከስልጣን እኛ ተገለልን ሲሆን ሌላው ደግሞ ነፍጠኛው በአቶ በረከት ፊተውራሪነት ወደፊት እየመጣ ነው የሚል ነው። ብአዴን ነው ነፍጠኛ እየተባለ ያለው እንግዲህ! እናንተዬ የኢህአዴግም ነፍጠኛ አለ ለካ! ልክ እንደ ክራይ ሰብሳቢነት ነፍጠኛም እየተዟዟረች ለጥቃት የሚጠቀሙባት ዱላ ነች። ኦሆዴድ ነፍጠኛ የሚለው አማራው በጠቅላላ የሚያስመስልበት ጊዜ አለ። ታዲያ ይህን የብአዴን ወደፊት መምጣት ያሰጋቸው የታችኛው ክፍል የህወሀት ሰዎች ውጭ ጉዳይ ሚንስትሩም ለብአዴን ሊሰጥ ነው እያሉ ሲስወሩ ሰነበቱ።

አንዱም ድንገት በሆነ ለቅሶ ቤት ተገናኝተን እንዲህ አለኝ “ለመሆኑ እናንተስ አላችሁ” አለኝ።

ጥያቄህ ፍልስፍናዊ ሆነኝ አልኩት፤ ጥያቄው “አንጃ ነን ያላችሁ የት አላችሁ” ዓይነት አድርጎ አቀረበው።

ዛሬ ነው እንዴ የታየንህ አልኩት በትዝብት። ይሄው ኤርትራዊው በረከት ስምኦን የትግራይን መሬት ለኤርትራ አሳልፎ ሊሰጥ አቆብቅበዋል። ”ባድሜ የእኛ አይደለችም” ብሏል፤ እንደገና ደግሞ አማራ ነኝ እያለ ነፍጠኛውን ከኋላው አሰልፎ ቤተ መንግስት ሊገባ ከበሩ ላይ ደርሷል። አሁን ደግሞ የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩን ቦታ ሊወስዱት ነው። እኔ ይሄ ነገር ከሆነ ይህ ሁሉ ጄኔራል ዝም ብሎ ያያል የሚል እምነት የለኝም። አለኝ አንድ ነገር ግልፅ ሆነልኝ ነፍጠኛው አሁንም በመንፈስ እየገዛን ነው ማለት ነው። ነፍጠኛው ግን ማነው ይህ ቃል እንደ ክራይ ሰብሳቢነት ለተለያዩ አላማ የሚጠብና የሚሰፋ ትርጉም አለው። በአቶ ስብሀት ነጋ የሚመራው አክራሪው የህወሀት ክንፍ ነፍጠኛ ማለት የሽዋው ስርዓት የሚመለከት ነው። ከዚያ ሲጠብ ደግሞ እስከሰሜን ሸዋ አንኮበር ድረስ ሊሆን ይችላል። አሁን ግን ብአዴንም ነፍጠኛ የሚባልበት ጊዜ ላይ ደረስንና ተገረምን።

ነገሩ ግን በህወሀት መንደር የተፈራው ሳይሆን ቀርቶ ዶር ዳኛቸው አሰፋ እንዳሉት “የሞትነውም እኛ ያለነውም እኛ” የሚል መልዕክት ያለው የስልጣን ሽግሽግ አድርጓል። በነገራቸን ላይ ዶ/ር ደኛቸው በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ህወሀት ተጠናክሯል በማለታቸው በፍልውሃው ሬዲዮ በእነ ሚሚ ስብሀቱ ፀረ ትግራይ መባላቸውን ሰማን። እንዴት ነው ነገሩ። ህወሀት ተጠናከረ ብሎ መናገር ፀረ ትግራይ የሚሆነው በየት አድርጎ ነው! ይህ ህወሀትና የትግራይን ህዝብ አንድ አድርጎ እንዲታይ ከመፈለግ የመጣ እርኩስ ሀሳብ ነው። ህወሀት ይህን ነገር እንዲሆንለት በጣም ይፈልጋል። አንዳንድ ተቃዋሚ ነኝ የሚሉ ጭፍን ግለሰቦችም እንደዚያ የሚያስቡ አሉ። ዶ/ር ዳኛቸው እንደዚያ እንደማያስቡ አውቃለሁ። እኔ እስከማውቀው ድረስ ግን የትግራይ ህዝብና ህወሀት ፈፅሞ አንድ አለመሆኑ ነው። ቢያንስ በሶስት ሊከፈል ይችላል፣ አንደኛ ህወሀት የሚደግፍ፣ ሁለተኛ አረና የሚደግፍ፣ ሶስተኛው ደግሞ ከሁለቱም ገለልተኛ የሆነ ህዝብ አለ። ስለዚህ ህወሀት የሚደግፈው ብቻ ነው የትግራይ ህዝብ መባል ያለበት የሚሉን ከሆነ ቁርጡን ይንገሩንና የሚሉትን ሁሉ እንቀበላቸው። ስለዚህ ህወሀት ተጠናክራል ማለት አንድም የሆነውን እውነታ መናገር ነው ይህ ደግሞ ፀረ ትግራይነት አይደለም።

ህወሀት ተጠናከረ ማለት ትግራይ ተጠናከረ ማለት አይደለምና። በአንፃሩ ህወሀት ተጠናከረ ማለት እንደሁልጊዜው በትግራይ ህዝብ ስም የመነገዱ ሁኔታ ተጠናክኖ ይቀጥላል ማለት ነው። እንደውነቱ ከሆነ ፀረ ትግራይ ማለት ባድሜ እኛ አይደለችም የኤርትራ ነች ብሎ መናገር ነው። ፀረ ትግራይ ማለት “አሰብ የእኛ አይደለም ማለት ነው። ምክንያቱም ኢትዮጵያ ወደብ አልባ ከሆነች የትግራይ ህዝብም ኢትዮጵያዊ በመሆኑ ወደብ አልባ ስለሚያደርገው ነው። ፀረ ትግራይ ማለት የአሉላም ስም እየፋቁ በመለስ መተካት ማለት ነው። ይህ ሁሉ እያደረጉ ያሉት ደግሞ ህወሀትና አቶ በረከት ስምኦን ናቸው። ይልቅ እነ ሚሚ ስብሀቱ እየተጠናከሩ ሊሆኑ ይችላሉ። ይሄው ካሁኑ ሰውዬው አስመራ ሊልኩት አይደለም። ኢሳይስን ይቅር በለን። የፈለከውን ሁሉ ከኢትዮጵያ ትወስድ ዘንድ መልካም ፍቃድህ ይሁን። ሊሉት አይደለም። መቼም ይሄ ከሰላም መፈለግ ጋር የሚያያዝ አይመስለኝም። ለዚህ ለዚህማ ከአሁን በፊት ለድርድር ዝግጅ ነን ማለታቸውን በቂ አልነበር። አቶ ኢሳይያስ ከኤርትራ ቴሌቭዥን በላይ በሚመለከቱት የአልጀዚራ ቴሌቭዥን ቀርበው ፍቃድ የማገኝ ከሆነ አስመራ ድረስ መምጣት እፈልጋለሁ ማለት ግን እጅግ በጣም የሚያሳፍር ተግባር ነው። ተቀብሎ ሳዋ ባይልካቸው ምን አለ በሉኝ!

ዞሮ ዞሮ አሁን ኢህአዴግ እየተረጋጋና እየተጠናከረ የሚሄድበት ጉደና የቀየሰ ይመስላል። የህዝቡ ጥያቄ በአንድ በእኩል አልተመለሰም። ተቀዋሚው ደግሞ ለዚህ ጊዜ የሚሆን አቅም አላጎለበተም። የህዝብ ጥያቄ እስካልተመለሰ ግን “ጉልቻ ቢለዋወጥ ወጥ አያጣፍጥም” የሚለው ገዥ ሀሳብ ነው እውነት የሚሆነው።

Advertisements
Categories: Articles
%d bloggers like this: