Home > TPLF woyane > የትግራይ ንግድ ምክር ቤት ከኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ራሱን ገነጠለ

የትግራይ ንግድ ምክር ቤት ከኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ራሱን ገነጠለ

December 27, 2012

የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔ ተራዘመ፣ –    የትግራይ ምክር ቤት ራሱን እንዳገለለ ነው

የትግራይ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ከኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት የሚደረግለትን ማንኛውንም ዓይነት ጥሪ ባለመቀበል ከብሔራዊ ንግድ ምክር ቤቱ ራሱን ማግለሉን ለማወቅ ተችሏል፡፡

በዳዊት ታዬ

የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ኅዳር 4 ቀን 2005 ዓ.ም. ለማካሄድ አቅዶት የነበረውን አምስተኛውን ጠቅላላ ጉባዔ ከሁለት ወር በላይ አራዘመ፡፡ በወይዘሮ ሙሉ ሰለሞን የሚመራው የምክር ቤቱ የዳይሬክተሮች ቦርድ ከአንድ ወር በፊት አምስተኛውን ጠቅላላ ጉባዔ የሚካሄድበትን ቀን በይፋ ማስታወቁ ይታወሳል፡፡ ሆኖም ጠቅላላ ጉባዔው የሚካሄድበት ቀን እንዲለወጥ ቦርዱ ድጋሚ ተሰብስቦ ጥር 16 ቀን 2005 ዓ.ም. እንዲካሄድ መወሰኑን የተገኘው መረጃ ያስረዳል፡፡

ጠቅላላ ጉባዔው ቀደም ብሎ የተያዘውን ፕሮግራም በመሰረዝ ከአንድ ወር በላይ ማራዘም ያስፈለገበት ምክንያት፣ ተደራራቢ ፕሮግራሞች በማጋጠማቸውና በተለይም የብሔራዊ ንግድ ምክር ቤቱ ጉባዔ መካሄድ ያለበት የምክር ቤቱ አባል የሆኑ ንግድ ምክር ቤቶች ቀድመው ጠቅላላ ጉባዔያቸውን ካካሄዱ በኋላ በመሆኑ ነው ተብሏል፡፡ ከምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ ጨምሮ እንደሚያስረዳው፣ ሁሌም አባል ምክር ቤቶች ጉባዔያቸውን ማጠናቀቃቸው ከታወቀ በኋላ የብሔራዊ ንግድ ምክር ቤቱ ጠቅላላ ጉባዔ የሚካሄድ በመሆኑ፣ አንዳንድ ምክር ቤቶች ጠቅላላ ጉባዔያቸውን ስላላካሄዱ ቀድሞ የተያዘው ፕሮግራም እንዲለወጥ ተደርጓል፡፡

ከአንዳንድ ወገኖች እየተደመጠ ያለው ግን ምክር ቤቱን እየመራ ያለው ቦርድ በአንድ ዓመት የሥራ ዘመኑ በተለይ በብሔራዊ ምክር ቤቱ ውስጥ በአባልነት ከታቀፉት 18 የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ውስጥ አንዳንዶቹ ከብሔራዊ ንግድ ምክር ቤቱ ጋር ያላቸው ግንኙነት ጤናማ ስላልነበር ይህንን ክፍተት ለመድፈን ጊዜ ለማግኘት ታስቦ ነው፡፡

በተለይ የትግራይ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አዲሱ ቦርድ ኃላፊነት ከተረከበ ወዲህ ከብሔራዊ ንግድ ምክር ቤቱ ጋር ያለው ግንኙነት መቋረጡን በምሳሌነት ያቀርባሉ፡፡ በአገሪቱ ውስጥ እየተንቀሳቀሱ ካሉ ንግድ ምክር ቤቶች ሁሉ በርካታ አባላትን በመያዝ በብሔራዊ ንግድ ምክር ቤቱ ውስጥ ከፍተኛ ድምፅ ያለው የትግራይ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ነው፡፡ ይህ ንግድ ምክር ቤት ከብሔራዊ ንግድ ምክር ቤቱ ጋር ልዩነት ከፈጠረባቸው ምክንያቶች መካከል አንዱ፣ የንግድ ምክር ቤቱ ሕንፃን በሚመለከት በአዲሱ ቦርድ የተወሰደው ዕርምጃ በዋናነት ይጠቀሳል፡፡ ሌሎች ልዩነት የተፈጠረባቸው ጉዳዮች እንዳሉም የሚናገሩ አሉ፡፡

ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች እንደሚጠቁሙት፣ ጠቅላላ ጉባዔው ከመካሄዱ በፊት በትግራይና በኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት መካከል ያለው ልዩነት በጠቅላላ ጉባዔው ላይ ጥያቄ እንዳያስነሳ ሲባል የተወሰደ ዕርምጃ ነው፡፡

የትግራይ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ከብሔራዊ ንግድ ምክር ቤቱ ጋር ያለውን ልዩነት ለማርገብ በቅድሚያ ሊደረግ ይገባል ያለውን አቋሙን በማሳወቅ ምላሽ እየተጠባበቀ የነበረ ቢሆንም፣ አወንታዊ ምላሽ ባለማግኘቱ ግንኙነቱ ሻክሮ ቆይቷል፡፡ ጉዳዩ በዚህ ሁኔታ በእንጥልጥል ከቆየ በኋላ የትግራይ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ከኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት የሚደረግለትን ማንኛውንም ዓይነት ጥሪ ባለመቀበል ከብሔራዊ ንግድ ምክር ቤቱ ራሱን ማግለሉን ለማወቅ ተችሏል፡፡

የብሔራዊው ንግድ ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔን ለማካሄድ ዝግጅት እየተደረገ ባለበት ወቅትም፣ የትግራይ ንግድ ምክር ቤት እንደማይሳተፍ ሲታወቅ ጉዳዩን በሽምግልና ለማርገብ ተደርጐ የነበረው ሙከራም ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

የብሔራዊ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ወይዘሮ ሙሉ ሰለሞን ለዚሁ ጉዳይ ወደ መቀሌ በማምራት ከትግራይ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አመራሮች ጋር ተገናኝተው ለመነጋገር ያደረጉት ሙከራ ያለመሳካቱንም ማረጋገጥ ተችሏል፡፡

የብሔራዊ ንግድ ምክር ቤቱ መረጃ ግን ጠቅላላ ጉባዔው ከአንድ ወር በላይ እንዲራዘም የተደረገበት ዋነኛ ምክንያት የክልልና የከተማ ንግድ ምክር ቤቶች ጠቅላላ ጉባዔ ሙሉ በሙሉ ባለመጠናቀቃቸው ነው ብሏል፡፡ አሁንም ገና ጠቅላላ ጉባዔያቸውን የሚያካሂዱ ንግድ ምክር ቤቶች ያሉ መሆኑንም ጠቁሟል፡፡

ጠቅላላ ጉባዔው የሚካሄድበት ቀን ቢለወጥም ከትግራይ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ጋር ተፈጠረ የተባለው ልዩነት የጠቅላላ ጉባዔው አጀንዳ መሆኑ እንደማይቀር ከንግድ ምክር ቤቱ አካባቢ የተገኙ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በቅርቡ አንድ የንግድ ምክር ቤቱ ቦርድ አባል ኃላፊነታችንን እንልቀቅ ብለው ያቀረቡት ጥያቄ መጪውን የብሔራዊ ንግድ ምክር ቤት ጠቅላላ ጉባዔ መሞገቱ አይቀርም ተብሏል፡፡

‹‹ከንግዱ ኅብረተሰብ የተሰጠንን ኃላፊነት በአግባቡ እየተወጣን አይደለም›› በሚል ከአንድ ሳምንት በፊት በተካሄደ የቦርድ ስብሰባ ኃላፊነታችንን እንልቀቅ ብለው ጥያቄ ያቀረቡት ከጋምቤላ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ተመርጠው በቦርዱ ውስጥ ሲያገለግሉ የቆዩ መሆናቸው ይታወሳል፡፡ ባሳለፍነው ሳምንት ኃላፊነታችንን መልቀቅ አለብን ብለው በግልጽ ለቦርዱ ባቀረቡት ደብዳቤ ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ በቦርዱ ነበሩ ያላቸውን በርካታ ችሮችን አንፀባርቀው ነበር፡፡ ይህ የቦርድ አባሉ ያልተጠበቀ ጥያቄ ቦርዱን ሳያስማማ መቅረቱም ታውቋል፡፡

source: http://ethiopianreporter.com/

Advertisements
Categories: TPLF woyane
%d bloggers like this: