Home > News > የትግሬው መንግስት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤ/ት እርቅ እንዲወርድ ሲጥሩ የነበሩትን ሊቀካህናት ኃይለሥላሴን ከሃገር በግዳጅ አስወጣ

የትግሬው መንግስት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤ/ት እርቅ እንዲወርድ ሲጥሩ የነበሩትን ሊቀካህናት ኃይለሥላሴን ከሃገር በግዳጅ አስወጣ

December 30, 2012

Fathers_in_Dallasከአገር ሽማግሌዎች ጋራ የተነጋገሩት ልኡካኑ መንግሥትን የመነጋገር ዕቅድም ነበራቸው

የዕርቅና ሰላም ተስፋው ክፉኛ እየተመናመነ ነው

የማክሰኞው የቅ/ሲኖዶስ ጉባኤ በወሳኝነት እየተጠበቀ ነው

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሰላምና አንድነት ጉባኤ ልኡክ በመኾን ወደ ኢትዮጵያ ከመጡት ሁለት ልኡካን አንዱ የኾኑት ሊቀ ካህናት ኀይለ ሥላሴ ዓለማየሁ ትላንት፣ ታኅሣሥ 19 ቀን 2005 ዓ.ም ምሽት ከኢትዮጵያ እንዲወጡ መደረጋቸው ተሰማ፡፡
በትላንትናው ዕለት ከቀትር በኋላ ፒያሳ ከሚገኘው መኖሪያቸው ‹‹ወደ ቦሌ ስብሰባ አለኝ›› ብለው ከወጡ በኋላ አለመመለሳቸው የተገለጸው ሊቀ ካህናት ኀይለ ሥላሴ ዓለማየሁ÷ ከአገር እንዲወጡ የተደረጉት በዚያው ቀን ምሽት ወደ አሜሪካ በሚበረው አውሮፕላን እንደኾነ ተነግሯል፡፡ ከእርሳቸው ጋራ አብረው ወደ ኢትዮጵያ የተጓዙት መ/ር አንዱዓለም ዳግማዊ በዚያው በአዲስ አበባ ቢኾኑም በምን ኹኔታ ላይ እንደሚገኙ ለማረጋገጥ አልተቻለም፡፡

በቀዳሚው ዘገባችን እንዳስነበብነው ሊቀ ካህናት ኀይለ ሥላሴ ዓለማየሁ የሰላምና አንድነት ጉባኤው ልኡክ በመኾን ወደ አዲስ አበባ የሄዱት ኅዳር 30 ቀን 2005 ዓ.ም በዳላስ ቴክሳስ በወጣው የሦስተኛ ዙር ጉባኤ አበው ውይይት÷ የጉባኤው ልኡካን ወደ ሁለቱም ወገኖቸ ምልአተ ጉባኤ ዘንድ በመሄድ ለአራተኛው ዙር የሎሳንጀለሱ ዕርቅና ሰላም ጉባኤ ስኬት የማግባባት ሥራ ለመሥራት ነበር፡፡ ኾኖም ልኡካኑ ወደ መንበረ ፓትርያሪኩ ቅጽር ገብተው ተልእኳቸውን እንዳይፈጸሙ ለጠቅላይ ቤተ ክህነቱ የጥበቃ አገልግሎት በተላለፈ መመሪያ መሠረት መታገዳቸውን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ሁለቱ ልኡካን ወደ መንበረ ፓትርያሪኩ ለመግባት ቢከለከሉም የደቡብና ምዕራብ አዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጵጵስናን ደርበው ከሚሠሩት የቅዱስ ሲኖዶስ ጸሐፊ ብፁዕ አቡነ ሕዝቅኤል ጋራ በአዲስ አበባ ሀ/ስብከት ተገኝተው መወያየታቸው ተዘግቧል፡፡ ውይይታቸው ካተኰረባቸው ጉዳዮች መካከል የሰላምና አንድነት ጉባኤው ያወጣውን መግለጫ በመቃወም የቅዱስ ሲኖዶሱ ዕርቀ ሰላም ልኡካን÷ የሰላምና አንድነት ጉባኤው ይቅርታ እንዲጠይቅና አካሄዱን እንዲያስተካክል ያወጡት ነው ስለተባለው መግለጫ እንደሚገኝበት ታውቋል፡፡

ብፁዕነታቸው ጉዳዩ የቅ/ሲኖዶሱ ዕርቅና ሰላም ልኡካን በቀጣይ ሳምንት ማክሰኞ ሪፖርት በሚያቀርቡበት ስብሰባ ሊታይ እንደሚችል ነግረዋቸዋል ተብሏል፡፡ ከዚህም ጋራ ተያይዞ ቀጣዩን የዕርቀ ሰላም ጉባኤ ስኬት በመወሰን ረገድ ወሳኝ አቋም የሚያዝበት፣ የ‹‹ዕርቀ ሰላም ይቅደም›› የሰላምና አንድነት ወገኖች – ‹‹የምርጫው ዝግጅት ይቀጥል፣ ዕርቀ ሰላሙም በተጓዳኝ ይካሄድ›› ከሚሉት የመንበረ ፕትርክና አላሚዎች አንገት ለይተው በሲኖዶሱ ጠረጴዛ ዙሪያ የሐሳብ ግብግብ የሚያደርጉበት የማክሰኞው የቅዱስ ሲኖዶሱ ስብሰባ በጉጉት እንዲጠበቅ አድርጎታል፡፡ የአስመራጭ ኮሚቴውን መቋቋም ከተቃወሙት የቅ/ሲኖዶሱ ሦስት የዕርቀ ሰላም ልኡካን ጋራ በአቋም የተለዩ ሌሎች የቅ/ሲኖዶሱ አባላትም ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መኾኑ ምርጫውን ለሚያስቀድሙት ጳጳሳት ከፍተኛ ስጋት አሳድሯል፡፡ የሰላምና አንድነት ጉባኤውን ልኡክ ከአገር የማባረር ርምጃ የተወሰደውም በማክሰኞው ጉባኤ በቅ/ሲኖዶሱ ፊት እንደሚቀርቡ የሚጠበቁት ሊቀ ካህናት ኀይለ ሥላሴ ዓለማየሁ ይህን ስጋት የሚያጠናክር የማሳመንና የማግባባት ሥራ እንዳይሠሩ ከወዲሁ ለማገድ ሊኾን እንደሚችል ተገምቷል፡፡ በብዙዎቹ አባቶች ምስክርነት ሊቀ ካህናት በጥቅምቱ የቅ/ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ፊት ቀርበው ባስረዱበትና ለቀረቡላቸውም ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት የነበራቸው ከፍተኛ የማሳመን ችሎታ ታይቷልና፡፡

ከመንበረ ፓትርያሪኩ በማገድ ተጀምሮ ትላንት ምሽት ከአገር በማስወጣት የተጠናቀቀውን የመንግሥት ርምጃ፣ አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች አቶ ስብሐት ነጋ በዚህ ሳምንት ታትሞ ከወጣው ሰንደቅ ጋዜጣ ጋራ በሰጡት ቃለ ምልልስ÷ ‹‹የአሜሪካው ሲኖዶስ›› ‹‹የእስልምና አክራሪዎችን እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ እንደሚደግፍ›› ከተናገሩት ክስና ‹‹አገር ውስጥ ያለው ሲኖዶስ የቤተ ክርስቲያኒቱ ህልውና ቆርቁሮት ድርጊቱን አላወገዘም፣ መንግሥትም ርምጃ አልወሰደም›› በሚል ካቀረቡት ወቀሳ ጋራ ያያዙታል፡፡ ይኸው የአቶ ስብሐት ክስና ወቀሳ የሰላምና አንድነት ጉባኤው ‹‹ለአሜሪካው ሲኖዶስ ይወግናል፤ የቅርቡ መግለጫም ይህን ያረጋግጣል›› በሚል የሚከሱ ጳጳሳትና ስም ያወጡ ግለሰቦች ግፊት ጋራ ተያይዞ ለርምጃው መድረሱ ተገምቷል፡፡

ጉዳዩ የቤተ ክርስቲያኒቱ አንድነትና ሰላም ጉዳይ እንጂ ሌላ አለመኾኑ፣ ይህም በውስጣዊ አሠራሯ ብቻ መፍትሔ ማግኘት የሚገባው መኾኑና መንግሥት በአፍኣ ኾኖ ድጋፍ የመስጠት ሚና ብቻ ነበር የሚጠበቅበት፡፡ የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴር በሰንደቅ ጋዜጣ እና በፋና ብሮድካስቲን ኮርፖሬት በኩል የነገረንም ይህንኑ ነበር፡፡ የሰላምና አንድነት ጉባኤው ሁለት ልኡካንም በያዙት መርሐ ግብር መሠረት ከዐሥሩ የአገር ሽማግሌዎች ቡድን አባላት ጋራ እንደመከሩት ሁሉ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ቢሮ እና የፌዴራል ጉዳዮች ሚኒስቴርን በዚሁ መንፈስ የማነጋገር ዕቅድ ነበራቸው ተብሏል፡፡ በቃል የቱንም ያህል ቢለፈፍ በተግባር ግሑድ እየኾነ ያለው ነገር የሕገ መንግሥቱን ቃልና መንፈስ የሚፃረር፣ አንድነትንና ሰላምን በዕርቀ ሰላም ለማረጋገጥ የተያዘውን ተስፋ ክፉኛ የሚያመነምን ነው፡፡

ምንጭ፡ www.zehabesha.com

Advertisements
Categories: News
%d bloggers like this: