Home > Uncategorized > የ “አማሮች ገለል በሉ ጉዳይ”: ታሪካዊ ስህተት ታሪክ የማይረሳው ዋጋ ያስከፍላል ከ አምደጺዮን

የ “አማሮች ገለል በሉ ጉዳይ”: ታሪካዊ ስህተት ታሪክ የማይረሳው ዋጋ ያስከፍላል ከ አምደጺዮን

January 5, 2013

ሁሉም ነገር ገደብ ያስፈልገዋል። ኢትጵያዊ ትህትና፣ ትዕግስት፣ ይሉኝታ፣ …… እና ሌሎች በመልካም ምግባርነት የሚወደሱ ሰብአዊ ባህሪዎች መልካምነታቸው አጠራጣሪ ባይሆንም ልክ ፣ ገደብ እና ሚዛን ….. ከሌላቸው ግን ስሜት አልባነትን ፣ ሙትነትን ፣ ፈሪነትን፣ ተሸናፊነትን፣ አጎብዳጅነትን …… ማመልከታቸው አይቀርም።

ዛሬ በሀገራችን በኢትዮጵያ ኢትዮጵያዊነት ከምንም በላይ አንገትን የሚያስደፋ ሆኗል። ኢትዮጵያዊነትን መግለፅ፣ የሚወዷትን ሀገር በመለያነት መጠቀም ወይም ኢትዮጵያዊ ነኝ ማለት ማስከበሩ ቀርቶ መዘለፊያ ሆኗል፤ “ትምክህተኛ” ለሚል ዘለፋ የሚዳርግ ፣ ለጥቃት የሚያጋልጥ ፣ ለእስር ፣ ለግድያ የሚያበቃ ፣ እንደ ሀገር አጥፊ ፣ እንደ መንግስት ጠላት እያስቆጠረ አንቀጽ የሚጠቀስበት ከሆነም ሁለት አስርት አመታት እንደዘበት ነጉደዋል። ይህ የኢትዮጵያን ህዝብ ብሔራዊ ስሜት የማኮላሸት ስትራቴጂ ባለፉት የህወሀት የሀያ አንድ አመታት የስልጣንና የአገዛዝ ዘመን ዋነኛ የፖለቲካ ስልት እና ዒላማ ሆኖ የህወሀትን ዕድሜ ለማራዘም ሁነኛ መሳሪያ ሆኖ አገልግሏል።

በዚህ በኩል በተለይ የአማራ ህዝብ የህወሀት ዋነኛ ዒላማ ሆኖ የአገዛዙን የግፍ ፅዋ ያለማቋረጥ እንዲጋት ሲደረግ ቆይቷል። ህወሀት የኢትዮጵያን ህዝብ ብሔራዊ ስሜት በማምከን ፣ የዘመናት ተገዥነቱን ለማረጋገጥ በቅድሚያ የአማራን ሕዝብ ማንነት ማጥፋት ፣ የአማራን ሕዝብ ስነልቦናዊ ጥንካሬ መስለብ እና አንገቱን ማስደፋት አስፈላጊ መሆኑን በጽናት ያምናል። ይህ በመሆኑም ፣ በአማራ ህዝብ ላይ በህወሀት የሚፈፀመው ግፍ እና በደል ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ስር እየሰደደና እየከፋ በግልፅም በስውርም በተቀነባበረ መንገድ ቀጥሏል።

ይህም ሆኖ አንዳንድ የዋህ ኢትዮጵያውያን ህወሀት በአማራ ህዝብ ላይ እየፈጸመ ያለውን ግፍና በደል ከአገዛዙ የመልካም አስተዳደር እጦት ጋር ለማያያዝ ይሞክራሉ። የህወሀት ጸረ ዲሞክራሲያዊ ባህሪ በአማራ ህዝብ ላይ የፈጠራቸው ሳንካዎች እንደሆኑ ሊያያሳምኑን ይጥራሉ። እውነቱ ግን ከዚህ በእጅጉ ይርቃል። የህወሀት አገዛዝ ከዲሞክራሲ ጋር በስም እንጂ በተግባር እንደማይተዋወቅ ጸሀይ የሞቀው እውነት ቢሆንም ፣ በአማራ ህዝብ ላይ እየተፈጸመ ያለው በደል ግን የራሱ የሆነ የተጻፈ አላማ ፣ ስትራቴጂ እና ግብ ያለው በመሆኑ ከዲሞክራሲም ሆነ ከመልካም አስተዳደር እጦት የተለየ ነው።

በሌላ በኩል ህወሀት ገና ከመነሻው የመጀመሪያዋን ጥይት ለመተኮስ ሲነሳ ዓላማየ ነው ብሎ በፅሁፍ ያሰፈረው ፕሮግራም በኢትዮጵያዊነት በተለይ ደግሞ በአማራ ህዝብ ላይ ያነጣጠረ በመሆኑ ‘”ታዲያ ይሄ ምኑ ይገርማል?’’ የሚል ጥያቄም የሚያነሱ አሉ። በእርግጥም የህወሀት ዓላማ የአማራን ህዝብ ማንበርከክ ፣ ባህሉን ፣ ምግባሩን፣ ታሪክ እና ህዝባዊ መሰረቶቹን መናድ መሆኑ በመመስረቻ መርሃግብሩ ላይ በግልጽ የሰፈረ፣ በድርጅቱ ዋና ዋና መሪዎች በግልጽ የሚቀነቀን በመሆኑ ምስጢር አልነበረም።

የአማራ ህዝብ ግን ይህን የህወሀት ግልፅ ጥላቻ እና ዓላማ እያወቀ ለጉዳዩ ብዙም ትኩረት ሳይሰጥ ፣ ለአፀፋ ምላሽም ሳይዘጋጅ አመታት አልፈዋል። ከዚህም አልፎ የአማራ ህዝብ ልጆች ከህወሀት ጐን በመሰለፍ “በሬ ካራጁ ይውላል” የሚለውን ብሂል የሚያስታውስ ስህተት ፈፅመዋል። በርግጥ ይህ ድርጊት ለአማራ ህዝብ አርቆ የማሰብ፣ የሀገርን ጥቅም የማስቀደም ፣ የወንድማማችነት ስሜትን የማጠናከር እርምጃ ተደርጎ ሊቆጠር ይችላል። ለህወሀት ሰዎች ግን ይህ ተላላነት ብቻ ሳይሆን ለሆድ አዳሪነት ፣ ለጥቅም ተገዢነት ነበር። ይህ በመሆኑም አብዛኞቹ የህወሀት አባላት ከጎናቸው የተሰለፉትን የአማራ ተወላጆች እንደ ትግል አጋር ለመቁጠር እጅግ ሲፀየፉ ማየት የተለመደ ነው። ስለሆነም የብአዴን አባላት ለትጥቅ ትግሉ የነበራቸውን አስተዋፅኦ ከማኮሰስ አልፈው “ሆዳም’’ በሚል ቅፅል ማሸማቀቅም በህወሀት የውስጥ ደንብ በህግ የተፈቀደ ነው የሚመስለው። በዚህም ምክንያት ፣ ትላልቅ የሚመስሉ ፣ የአማራን ስም የያዙ ፣ በብአዴን ከፍተኛ አመራርነት የሚታወቁ፤ በከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊነት ላይ በአካል የሚታዩ ሹማምንት በተራ የህወሀት አባላት ሲብጠለጠሉ ፣ ሲዘለፉ ፣ የስራ መመሪያ ሲሰጣቸውና ሲቀበሉ ማየት የሚያስደንቅ አይደለም።

አባቶቻችን መረን የለቀቀ ነገር ሲገጥማቸው እና ጉዳዩ በወቅቱ ካልታረመ ሊያመጣ የሚችለውን ችግር ሲገነዘቡ “ይህች ባቄላ ካደረች አትቆረጠምም” ይሉ ነበር። የእኛ ትውልድ ግን ይህችን የአባቶች ምክር በመዘንጋት ህወሀት አማራን በጠላትነት ፈርጆ ጠመንጃ ሲያነሳ፣ ውሎ አድሮ ከጊዜ በኋላ ሊያስከትል የሚችለውን ጠንቅ ባለመገንዘብ ለፀፀት የሚዳርግ ስህተት ፈፅሟል። ከዚህ አልፎም ለህወሀት የጸረ አማራ ትግል ህይወቱን ጭምር እየገበረ መሳሪያ በመሆን አገልግሏል። አሁንም በፍፁም የተገዥነት (የሎሌነት) ስሜት በራሱ ወገኖች ጥቅም ፣ ህልውና እና ክብር ላይ ለሚፈፀመው በደል በፊታውራሪነት በማገልገል ላይ ይገኛል።

ህወሀት በአማራ ህዝብ ላይ ያለውን የጠላትነት ስሜት ለመወጣት በቅድሚያ መሳሪያ ያደረገው በአማራ ህዝብ ላይ አሉታዊ የሆነ ሰፊ የፕሮፓጋንዳ ስትራቴጂ በመንደፍ ነበር። በብቸኝነት የሚቆጣጠራቸውን የመንግስት መገናኛ ብዙሀን የአማራን ህዝብ ስም ለማጠየም ብቻ ሳይሆን ለማጥቆር ፣ በሌሎች ብሄሮችና ብሄረሰቦች ዘንድ ስለ አማራ ህዝብ ያለውን በጎ አመለካከት በማጥፋት በጥላቻ ለመተካት ያለመታከት ሰርቷል። የአማራ ህዝብ ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ የተለየ ጥቅም ሲያገኝ እንደኖረ ፣ ሌሎች ብሄር ብሄረሰቦችን ሲጨቁንና ሲገዛ ዘመናትን እንዳስቆጠረ ፣ ለሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች ባህል ፣ እምነት እና አስተሳሰብ ከፍተኛ ንቃት እንዳለው የሚያሳዩ የተቀነባበሩ የፕሮፓጋንዳ ዘመቻዎችን በማካሄድ ታሪክ የማይረሳው በደል ፈፅሟል፤ አሁንም በመፈጸም ላይ ይገኛል።

ይህ የህወሀት የጸረ አማራ ፕሮፓጋንዳ ማሽን የሚ’መራው ፣ “ሆድ ሲያውቅ ደሮ ማታ” እንደሚሉት ቢሆንም አማራ ነኝ በሚሉት ነገር ግን በአማራ ህዝብ ላይ ጅምላ ጨራሽ የፕሮፓጋንዳ መርዝ በመርጨት በሚታወቁት አቶ በረከት ስምዖን ነው። የህወሀት የጸረ አማራነት አቋም እጅግ የከፋ ፣ ስር የሰደደ እና የሰረጀ በመሆኑ በኢትዮጵያ አንድነት የፀና እምነት እንዳላቸው የሚገልጹ የሌሎች ብሄር ብሄረሰቦች ተወላጆችን ጭምር የአማራ መለያ እየሰጠ፣ “ትምህክተኛ” የሚል ስድብ እየመረቀ አንገታቸውን እንዲደፉ እስከማድረግ ደርሷል። አሜሪካዊው ምሁር ዶናልድ ሌቪን ህወሀት በ1997 በተካሄደው ምርጫ በህዝብ ድምጽ ተሸንፎ ስልጣኑን በጉልበቱ እንደተቆጣጠረ በመዝለቁ በሀገሪቱ የተፈጠረውን ቀወስ ለመሸምገል ሟቹን ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ሲያነጋግሩ የተሰጣችው ምላሽ ለዚህ ሁነኛ ማሳያ ይሆናል። በወቅቱ ጠ/ሚንስትሩ በምርጫው ውጤት መሰረት ለምን ስልጣኑን እንደማይለቁ ወይም እንደማያጋሩ ሲጠየቁ “እኛ ለአማራ ስልጣን አንለቅም” የሚል ምላሽ መስጠታችው ተሰምቶአል። “ቅንጂት እኮ የአማራ ድርጅት አይደለም ትግሬዎችም አሉበት” ሲባሉ የሰጡት ምላሽ ደግሞ አቶ መለስ ምን ያህል የአማራ ጥላቻ ናላቸውን እንዳዞረው የሚያሳይ ይሆናል። “ናዚ ውስጥም አይሁዶች ነበሩበት” ነው መልሳቸው። የአማራን ህዝብ ከማን ጋር እንዳነጻጸሩት ማሰብ ፣ ይህን የመረረና ስር የሰደደ ጥላቻ ይዘው በሚመሩት አገር የአማራ ህዝብ ምን ሊደርስበት አንደሚችል መገመት ይቻላል። ባለፉት 21 በአማራ ህዝብ ላይ በህወሀት የተፈፀመው ግፍ እና በደል መንስኤን ከዚህ መገንዘብም አያዳግትም።

ህወሀት በገዢነት በቆየባቸው ዓመታት በአማራ ህዝብ ላይ እየፈፀመ ያለው በደል በፕሮፓጋንዳ ላይ ብቻ የተወሰነም አልነበረም። በሺዎች የሚቆጠሩ የአማራ ልጆች ኢትዮጵያዊነታቸውን በመግለፃቸው ብቻ ለግድያና አፈና ተዳርገዋል። ህወሀትን ይቃወማሉ ተብለው በመጠርጠራቸው ብቻ የዜግነት መብታቸውን የተነፈጉ ፣ ኢኮኖሚያዊ ጥቅማቸውን የተነጠቁ፣ ከመኖረያ ቀያቸው የተፈናቀሉ ፣ የአማራ ተወላጆች ቁጥር በቀላሉ የሚገመት እንዳልሆነም በየጊዜው በሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች የሚወጡትን ሰነዶች በመፈተሽ ማረጋገጥ ይቻላል። ከወረዳ አስከፌደራል ባሉት አስር ቤቶች ለወጉ እንኳን ለፍርድ ሳይቀርቡ እና የሰሩት ወንጀል ሳይገለጽላችው በእስር የሚማቅቁ ዜጐች ቁጥርም ቀላል አይደለም።

በአሁኑ ወቅት ይህ ከሀያ አመታት በላይ በአማራ ህዝብ ላይ ያለማቋረጥ በገዥው የህወሀት መንግስት እየተካሄደ ያለው የፕሮፓጋንዳና እና የጥቃት ዘመቻ ሳያንስ ይህንን ቅኝት ተከትሎ የመሄድ አዝማሚያ በየቦታው መታየት መጀመሩ ደግሞ “በእንቀርት ላይ ጆሮ ደግፍ” እንዲሉ ይበልጥ ያሳስባል።

የህወሀትን መንገድ ተከትሎ አማራን እንደዘመናት ገዥ የመቁጠር ፣ በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ በየዘመኑ በነበሩ መንግስታት ለተፈፀመው በደል ተጠያቂ አድርጎ የማቅረብ አዝማሚያ ተቃዋሚ ነን በሚሉ ወገኖች ጭምር ሲንፀባረቅ መሰማቱ የህወሀት የዘመናት ጥረት ለፍሬ መብቃቱን የሚያሳይ የማንቂያ ደውል መሆኑን መገንዘብም ያስፈልጋል። ውሸት ሲደጋገም ውነት ይመስላል ነው ነገሩ።

ከመነሻው በዘር ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ ለአንድ ሀገር እድገት ፣ ልማት እና የዲሞክራሲ ባህል መጠናከር አሉታዊ አስተዋፅኦ እንዳለው ተገንዝበው ህብረ ብሄራዊ የፖለቲካ ድርጅት ያዋቀሩ አካላት “የአማራ ድርጅት ታስብሉናላችሁ” በሚል ሰበብ የአመራር ምርጫ ሲያካሂዱ “አማሮች ገለል በሉ” የሚል አቋም መያዝ መጀመራቸውና የአማራ ተወላጆችም ይህን ተቀብለው ለትግሉ ያላቸው አስተዋፅኦ ሳይጓደል ገለል ለማለት መፍቀዳቸው እጅግ አሳፋሪ ብቻ ሳይሆን አሳሳቢም ይሆናል።

የአማራ ህዝብ በሀገሩ ጉዳይ ላይ የሚያሳፍርም ሆነ አንገት የሚያስደፋ ታሪክ የለውም። የሀገሩን ሉዐላዊነት ለማስከበር፣ ከመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር ወገን ሳይለይ በግንባር ተሰልፎ ደሙን አፍሷል፣ ውድ ህይወቱን ገብሯል። “ከሀገሬ በፊት እኔን” ብሎ በዱር በገደሉ ወድቆ ቀርቷል። ለሀገሩ ሉዐላዊነት ፣ ክብርና ሞገስ የሚገባትን ዋጋ ሲከፍል ኖሯል፡፡ ስለዚህ የአማራን ህዝብ በሀገሩ ጉዳይ “ገለል በል” ሊለው የሚደፍር ካለ እሱ ኢትዮጵያዊ ያልሆነ ወይም አሰላለፉ ከጠላት ወገን የነበረ ብቻ ነው።

ይህ ሁኔታ የአማራ ህዝብ ከሀያ አመታት በላይ የተፈፀመበት በደል ፣ በህወሀት አባላት ብቻ ሳይሆን በአማራ ስም ለወያኔ ባደሩ ልጆቹ ጭምር መሆኑን ማስታወስ እንደሚያስፈልግ ይጠቁማል። ከመነሻው የሽግግር መንግስቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አቶ ታምራት ላይኔ ከአማራ ተወለድኩ ፣ አማራን እወክላለሁ እያሉ ፀረ አማራ ፕሮፓጋንዳ ሲነዙ እንደ ነበር ማስታወስ ያስፈልጋል። ቢያንስ ቢያንስ ወደምስራቅ ኢትዮጵያ ወርደው ‘’ወገቡን ተመትቶ የነበረው አማራ አንገቱን ቀና እያደረገ ነው፣ ……. አማሮችን በሏቸው” የሚለው “ጆሮ ገብ” ንግግራቸውን ተከትሎ በአማሮች ላይ የደረሰውን መፈናቀል ፣ ግድያና ጥቃት እንዴት መርሳት ይቻላል?

በ 1997 ታሪካዊ ምርጫ ወቅት ቅንጅት መሬትን የግል ሀብት ማድረግን እንደ አንድ አማራጭ ማቅረቡን ለመቃወም አማራን ወክያለሁ የሚሉት አቶ በረከት ስምዖንና ጓዶቻቸው በደቡብ ኢትዮጵያ ሲቀሰቅሱ ኢላማ ያደረጉት እንደተለመደው የአማራን ህዝብ ነው። “መሬት የግል ሀብት እንዲሆን በፖሊሲ ከተፈቀደ መሬታችሁን አማራና ጉራጌ ይነጥቋችኋል” በማለት ህወሀት ፖሊሲ ሲያወጣ እንኳን አማራን ለመቃወም ወይም ለመቃረን ቅድሚያ እንደሚሰጥ አረጋግጠውልናል። ይህ አቋም የአቶ በረከት ብቻ ሊሆን ይችላል ብለን እንዳንጠራጠር አሜሪካዊው ዲፕሎማት ኸርማን ኮህን በአንድ ወቅት ከሟቹ ጠ/ሚኒስትርና የህወሀት መሪ አቶ መለስ ዜናዊ ጋር በነበራቸው ቆይታ መሬትን የግል ሀብት የማድረግ አማራጭን መንግስታቸህው ለምን እንደማይቀበል ላቀረቡላቸው ጥያቄ የህወሀቱ ቁንጮ መለስ ዜናዊ “መሬት በአማሮች እጅ ይገባና ወደ ነበርንበት የጭሰኝነት ስርአት ይመልሰናል” የሚል መልስ በመስጠት ጸረ አማራነታቸውን ግልጽ አድርገዋል።

በተጨማሪም የህወሀት መስራች አባትና ስትራተጂስት የሆኑት ስብሀት ነጋ ‘’ከአማራ ስልጣን ነጥቀን ….. ለደቡብ ሰጥተናል” ብለው መግለጫ መስጠታቸውን የሰማ ማንም ሰው የአማራ ህዝብ በኢትዮጵያ ውስጥ እየተፈፀመበት ያለውን ግፍና በደል ማወቅ አይሳነውም። የኢትዮጵያ መከላለያ ሰራዊትን የሚመሩት ኢታማዥር ሹም ጀነራል ሳሞራ የኑስ በአንበሳ ባንክ ምስረታ ጉባኤ ላይ ተገኝተው “ገድለን የቀበርነውን አማራ አታስነሱብን” ማለታቸው መሰማቱ ደግሞ ከያዙት ሀላፊነት አንፃር የአማራ ህዝብ በቅኝ ተገዥነት ስር መውደቁን ለመመልከት ከበቂ በላይ ነው። ይህ ሰው በአቶ መለስ ትእዛዝ በ 1997 ምርጫ ማግስት ከ 200 በላይ ድምፃችን ይከበር ብለው የጠየቁ ዜጎችን ያለርህራሄ የጨፈጨፈውን ጦር በበላይነት የሚመሩ መሆኑን ስናስታውስ የህወሀት ጥላቻ በአማራ ህዝብ ላይ እስከምን ድረስ ሊሄድ እንደሚችል ብንሰጋ አይፈረድብንም።

ባጠቃላይ ህወሀት የለየለት የአማራ ህዝብ ጠላት መሆኑን አመራሮቹ ያለ ሀፍረት በአደባባይ ደጋግመው ነግረውናል። ዛሬ ኢትዮጵያ የምትባለው ሀገር ለአማራ ህዝብ የበደል ፅዋ የሚጨለጥባት ብቻ አይደለችም። የአማራ ህዝብ ተሸማቆ ፣ አንገቱን ደፍቶ፣ የገዥዎቹን የግፍ አገዛዝ አሜን ብሎ ተቀብሎ የሚኖርባት ሆናለች። ኢትዮጵያ የእኔ ናት የሚለውን እምነቱን ተነጥቆ ፣ በተሸናፊነት አንገቱን ደፍቶ ፣ በእፍረትና በውርደት የሚኖርባት ሀገር መሆኗን ለማወቅም አማራ መሆንን አይጠይቅም።

በመሆኑም ዛሬ የአማራ ህዝብ ህልውና እጅግ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ ወድቋል ማለት ይቻላል። ይህም ሆኖ የአማራን ህዝብ ሰነድ ቀርፆ ጠላትነቱን በግልፅ አስቀምጦ ይህንኑም በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ በተግባርም በፕሮፓጋንዳም በማረጋገጥ ላይ ከሚገኘው ከህወሀት ይልቅ የራሱ ልጆች እየፈፀሙበት ያለው በደል እጅግ ያሳስባል። በመሆኑም በስሙ ተደራጅተው ገለል በሉ ሲባሉ አሜን ብለው የሚቀበሉ አጐብዳጆች ለዘመናት በወያኔ ሲነዛ ለነበረው ፀረ አማራ ፕሮፓጋንዳ እጅ መስጠታቸውን ሊያስታውሱ ይገባል።

የአማራ ህዝብ እንደማንኛውም የኢትዮጵ ህዝብ በድህነት ፣ በጉስቁልና ፣ በመልካም አስተዳደር እጦት ሲንገላታ የኖረ ህዝብ ነው። የአገሩን ዳር ድንበር ለማስከበር፣ ነፃነቷን ለማረጋገጥ፤ ወንዝ፣ ተራራ ሳይበግረው ፣ የጎሳና የዘር ድንበር ሳይከልለው፤ ደሙን ሲያፈስ፣ ህይወቱን ሲገብር ነው የኖረው። ይህም ሆኖ ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ ከአማራ ህዝብ በላይ በድህነት የሚቀጣ ፣ በዲሞክራሲ እጦት ለመከራ የተዳረገ ህዝብ አለ ብሎ ማመን ያስቸግራል። ስለሆነም የወያኔን የፕሮፓጋንዳ ፈለግ ተከትሎ ከበሮ የሚደልቅ የፖለቲካ ድርጅት በመርዛም ጥላቻ እና ዘረኝነት ከተዘፈቀው የህወሀት አመራር ያልተሻለና በዘቀጠ አስተሳሰብ የተማረከ መሆኑን ልብ ሊል ይገባል። ምክንያቱም ይህ ለዘመናት የተካሄደ ፕሮፓጋንዳ በዚህ መንገድ ተቀባይነት እንዲያገኝ መፍቀድና እውቅና መስጠት የሚያስከትለው ጠንቅ እንዲህ በቀላሉ ሊታይ እንደማይገባ ከታሪክ መማር አለብን።

ይህን በሚመለከት ሟቹ ጠ/ሚኒስትር በማነጻጸሪያነት ናዚዝምን ማቅረባቸውን ከግምት ውስጥ በማስገባት ታሪኩን መመርመር ያስፈልጋል። በርግጥም በናዚነት የተወገዘው ሂትለር ፣ በአይሁዶች ላይ የነበረው ጥላቻ ከመነሻው ለ ስድስት ሚሊዮን አይሁዶች እልቂት ምክንያት ይሆናል ብሎ ያሰበ ማንም አልነበረም። ሂትለር እንደ አቶ መለስ ፤ እንደ ጄነራል ሳሞራ ፤ እንደ አቶ ስብሀት ነጋ ፤ … አንድ ሰው ነበር። በአይሁዶች ላይ የነበረው ጥላቻ ግን እጅግ የመረረና ስር የሰደደ ብቻ ሳይሆን ለሌሎች ሊተርፍ የሚችልም ሆኗል። ነገር ግን ይህ ብቻውን ስድስት ሚሊዮን አይሁዶችን ለመጨፍጨፍ በቂ አልነበረም። ሂትለር የመንግስት ስልጣንን ሲጨብጥና ይህን ጥላቻውን ወደሌሎች ማስተላለፍ የሚችልበትን የፕሮፓጋንዳ መሳሪያ ሲቆጣጠር ፤ ከዚያም አልፎ በዓለም ላይ ጠንካራ የሚባል ሰራዊትን በባለቤትነት ሲመራ ግን የሆነውን አይተናል። ሂትለር ያስከተለውን እልቂት ዛሬ ላይ ሆነን ስናስተውል ፣ የአማራ ህዝብ ህልውና በህወሀት እየተፈተነ መሆኑን እንገነዘባለን።

የህወሀት መሪዎችን ከዚህ አንጻር እንመልከታቸው። መለስ ዜናዊ ፣ ሳሞራ የኑስ ፣ ስብሀት ነጋ፣ በረከት ስምዖን ወ.ዘ.ተ. በአማራ ህዝብ ላይ አስከአሁን ከፈጸሙት በላይ ጥፋት ለመፈጸም የሚያበቃ ጥላቻ አላቸው ወይ? የሚለውን ጥያቄ ለራሳችን እናቅርብ። እነርሱ ደግመው ደጋግመው፣ ማንን እንፈራለን ብለው፣ “አዎ!” ብለውናል። ስለዚህ የመጀመሪያውንና ትልቁን መስፈርት አሟልተዋል። የአማራን ህዝብ እንደ ህዝብ ለማጥቃት ፣ ባህሉን ፣ ማንነቱን ፣ አስተሳሰቡን እና ብሄራዊ ኩራቱን ለማጥፋት የሚያስችል በቂ ጥላቻ እና ቂም ቋጥረዋል። ስለዚህ ቀሪው ነገር ይህን ለመፈጸም የሚያስችል በቂ አቅም አላችው ወይ? የሚለው ነው። በርግጥም አንደሂትለር ሁሉ ፣ የመንግስትን ስልጣን ጨብጠው ላለፉት ሃያ አንድ አመታት አገሪቱን ገዝተዋል። በድርጅታቸው አባላት ቁጥጥር ስር የሆነ ፣ የሃይል ሚዛኑ እጅግ ወደ አንድ ወገን ያዘነበለ፣ በተመሳሳይ ርዕዮትና የፖለቲካ አስተሳሰብ የተቃኘ ሰራዊትም ገንብተዋል። በዚህ ላይ ከአማራ ህዝብ የወጡ ወዶ ገቦችን ይዘዋል። ይህን እኩይ ሀሳባቸውን የሚያሰራጩበት እና የኢትዮጵያን ህዝብ አማራጭ መረጃዎችን የማግኘት ዕድሉን የሚያፍኑበት ሰፊና ብቸኛ የመገናኛ ብዙሃን ባለቤትነታቸውንም አረጋግጠዋል። ምን ቀረ?…. አስተዋይ አእምሮ ይስጠን፤ ምክንያቱም ዛሬ ላይ ይህን መረን የወጣ አንባገነንነት ፤ የከፋ ዘረኝነት ፤ ግፍ እና በደል በቸልታ መመልከት ሊያስከፍል የሚችለውን በደል ካለመገንዘብ ሳይሆን ከባርነት ጋር ከመላመድ ብቻ ነው ሊመጣ የሚችለው።

Advertisements
Categories: Uncategorized
%d bloggers like this: